በዚያ ዘመን ይላል እግዚአብሔር፤ ለእስራኤል ወገኖች ሁሉ አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከሰይፍ የተረፈው ሕዝብ በምድረ በዳ ሞገስ አገኘ። ሂዱ፦ እስራኤልንም አታጥፉ።” እግዚአብሔርም ከሩቅ ተገለጠልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በዘለዓለም ፍቅር ወድጄሃለሁ፤ ስለዚህ በቸርነት ሳብሁህ። የእስራኤል ድንግል ሆይ እንደ ገና እሠራሻለሁ፤ አንቺም ትሠሪያለሽ፤ እንደ ገናም ከበሮሽን አንሥተሽ ከዘፋኞች ጋር ትወጫለሽ። እንደ ገናም በሰማርያ ተራሮች ላይ የወይን ተክሎችን ትተክሊአለሽ፤ የምትተክሉ ትከሉ፤ አመስግኑም፤ በኤፍሬም ተራሮች ላይ የሚከራከሩ፦ ተነሡ፤ ወደ ጽዮን ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር እንውጣ ብለው የሚጠሩባት ቀን ትመጣለችና።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፥ “የያዕቆብ ቤት ሆይ! ደስ ይበላችሁ፤ በአሕዛብም አለቆች ላይ እልል በሉ፤ አውሩ፤ አመስግኑም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን የእስራኤልን ቅሬታ አድኖአል በሉ። እነሆ፥ ከሰሜን ሀገር አመጣቸዋለሁ፤ ከምድርም ዳርቻ ለበዓለ ፋሲካ እሰበስባቸዋለሁ፤ ብዙ አሕዛብም ይወለዳሉ፤ ወደዚህም ይመለሳሉ። እያለቀሱ ሄዱ፤ እኔም በማጽናናት አመጣቸዋለሁ፤ በወንዝ ዳር በቅን መንገድ አስሄዳቸዋለሁ፤ በእርሱም አይሰናከሉም፤ እኔ ለእስራኤል አባት ነኝና፥ ኤፍሬምም በኵሬ ነውና።” አሕዛብ ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና፥ “እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል፤ እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ። እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል፤ ከበረቱበትም እጅ አድኖታል። ይመጣሉ፤ በጽዮንም ተራራ ደስ ይላቸዋል፤ ወደ እግዚአብሔርም በጎነት፥ ወደ እህልና ወደ ወይን ጠጅ፥ ወደ ዘይትም፥ ወደ በጎችና ወደ ላሞች ሀገርም ይሰበሰባሉ፤ ነፍሳቸውም እንደ ረካች ገነት ትሆናለች፤ ከእንግዲህም ወዲህ አይራቡም። በዚያን ጊዜም ደናግሉ በዘፈን ደስ ይላቸዋል፤ ጐበዛዝቱና ሽማግሌዎቹም በአንድ ላይ ደስ ይላቸዋል፤ እኔም ልቅሶአቸውን ወደ ደስታ እመልሳለሁ፤ ከኀዘናቸውም ደስ አሰኛቸዋለሁ። የካህናቱንም የሌዊን ልጆች ሰውነት ከፍ ከፍ አደርጋታለሁ፤ አረካታለሁ፤ ሕዝቤም ከበረከቴ ይጠግባል፥” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የኀዘን፥ የልቅሶና የጩኸት ድምፅ በራማ ተሰማ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፤ የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ድምፅሽን ከልቅሶ፥ ዐይኖችሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ። ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። “ኤፍሬም ሲጨነቅ መስማትን ሰማሁ፤ እንዲህም አለ፦ ቀጣኸኝ እኔም እንዳልቀና ወይፈን ተቀጣሁ፤ አንተ እግዚአብሔር አምላኬ ነህና መልሰኝ፤ እኔም እመለሳለሁ። ከተመለስሁ በኋላ ተጸጸትሁ፤ ከተገሠጽሁም በኋላ ጭኔን ጸፋሁ፤ የብላቴንነቴንም ስድብ ተሸክሜአለሁና አፈርሁ፥ ተዋረድሁም። በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የተወደደ ልጅ ነው፤ ደስ የሚያሰኝም ሕፃን ነው፤ በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቍጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት፤ ርኅራኄም እራራለታለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር። “ለራስሽ የመንገድ ምልክት አድርጊ፥ መንገድንም የሚመሩ ዐምዶችን ትከዪ፤ ልብሽንም ወደ ሄድሽበት መንገድ ወደ ጥርጊያው አቅኚ፤ አንቺ የእስራኤል ድንግል ሆይ! ተመለሺ፤ ወደ እነዚህም ወደ ከተሞችሽ እያለቀስሽ ተመለሺ። አንቺ ከዳተኛ ልጅ ሆይ! እስከ መቼ ትቅበዘበዣለሽ? እግዚአብሔር በምድር ላይ አዲስ ነገር ፈጥሮአልና ሰው ወደ ድኅነት ይመጣል።”
ትንቢተ ኤርምያስ 31 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 31:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች