ትን​ቢተ ኤር​ም​ያስ 10:1-16

ትን​ቢተ ኤር​ም​ያስ 10:1-16 አማ2000

እና​ንተ የእ​ስ​ራ​ኤል ቤት ሆይ! እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በእ​ና​ንተ ላይ የተ​ና​ገ​ረ​ውን ቃል ስሙ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “የአ​ሕ​ዛ​ብን መን​ገድ አት​ማሩ፤ ከሰ​ማይ ምል​ክ​ትም አት​ፍሩ፤ አሕ​ዛብ ከእ​ነ​ርሱ የተ​ነሣ ይፈ​ራ​ሉና። የአ​ሕ​ዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፥ ከዱር በመ​ጥ​ረ​ቢያ እን​ደ​ሚ​ቈ​ረጥ፥ በሠ​ራ​ተ​ኛም እጅ እን​ደ​ሚ​ሠራ እን​ጨት ነው። በብ​ርና በወ​ርቅ ይለ​ብ​ጡ​ታል፤ እን​ዳ​ይ​ና​ወ​ጥም በች​ን​ካ​ርና በመ​ዶሻ ይቸ​ነ​ክ​ሩ​ታል። እንደ ተቀ​ረጸ ብር ናቸው፤ እነ​ር​ሱም አይ​ና​ገ​ሩም፤ መራ​መ​ድም አይ​ቻ​ላ​ቸ​ው​ምና ይሸ​ከ​ሙ​አ​ቸ​ዋል። ክፉ መሥ​ራ​ትም አይ​ቻ​ላ​ቸ​ው​ምና፥ ደግ​ሞም መል​ካም ይሠሩ ዘንድ አይ​ች​ሉ​ምና አት​ፍ​ሩ​አ​ቸው።” አቤቱ! እንደ አንተ ያለ የለም፤ አንተ ታላቅ ነህ ስም​ህም በኀ​ይል ታላቅ ነው። የአ​ሕ​ዛብ ንጉሥ ሆይ! በአ​ሕ​ዛብ ጥበ​በ​ኞች ሁሉ መካ​ከል፥ በመ​ን​ግ​ሥ​ታ​ቸ​ውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለ​ሌለ፥ ለአ​ንተ ክብር ይገ​ባ​ልና አን​ተን የማ​ይ​ፈራ ማን ነው? በአ​ንድ ጊዜ ሰን​ፈ​ዋል፥ ደን​ቍ​ረ​ው​ማል፤ ጣዖ​ታት የሚ​ያ​ስ​ተ​ም​ሩት የእ​ን​ጨት ነገር ብቻ ነው። የሠ​ራ​ተ​ኛና የአ​ን​ጥ​ረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተ​ር​ሴስ ጥፍ​ጥፍ ብር፥ ከአ​ፌ​ዝም ወርቅ ይመ​ጣል፤ ልብ​ሳ​ቸ​ውም ሰማ​ያ​ዊና ቀይ ግምጃ ነው፤ ሁሉም የብ​ል​ሃ​ተ​ኞች ሥራ ናቸው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ግን እው​ነ​ተኛ አም​ላክ ነው፤ እር​ሱም ሕያው አም​ላ​ክና የዘ​ለ​ዓ​ለም ንጉሥ ነው፤ ከቍ​ጣው የተ​ነሣ ምድር ትን​ቀ​ጠ​ቀ​ጣ​ለች፤ አሕ​ዛ​ብም መዓ​ቱን አይ​ች​ሉም። እና​ን​ተም፦ ሰማ​ይ​ንና ምድ​ርን ያል​ፈ​ጠሩ እነ​ዚህ አማ​ል​ክት ከም​ድር ላይ፥ ከሰ​ማ​ይም በታች ፈጽ​መው ይጥፉ ትሉ​አ​ቸ​ዋ​ላ​ችሁ። ምድ​ርን በኀ​ይሉ የፈ​ጠረ፥ ዓለ​ሙን በጥ​በቡ ያጸና፥ ሰማ​ያ​ት​ንም በማ​ስ​ተ​ዋሉ የዘ​ረጋ እርሱ ነው። በላይ በሰ​ማይ ውኆ​ችን ይሰ​በ​ስ​ባል፤ ከም​ድ​ርም ዳርቻ ደመ​ና​ትን ከፍ ያደ​ር​ጋል፤ ለዝ​ና​ብም መብ​ረ​ቅን ያደ​ር​ጋል፤ ነፋ​ስ​ንም ከቤተ መዛ​ግ​ብቱ ያወ​ጣል። ሰው ሁሉ ዕው​ቀት አጥቶ ሰን​ፎ​አል፤ አን​ጥ​ረ​ኛም ሁሉ ከቀ​ረ​ጸው ምስል የተ​ነሣ አፍ​ሮ​አል፤ ቀልጦ የተ​ሠራ ምስሉ ውሸት ነውና፥ እስ​ት​ን​ፋ​ስም የለ​ው​ምና። አገ​ጣ​ጥ​መው የሚ​ሠ​ሩት ሥራ ከንቱ ነው፤ በተ​ጐ​በኙ ጊዜም ይጠ​ፋሉ። የያ​ዕ​ቆብ ዕድል ፈንታ እንደ እነ​ዚህ አይ​ደ​ለም፤ እርሱ ሁሉን የፈ​ጠረ ነውና እስ​ራ​ኤ​ልም የር​ስቱ ነገድ ነውና፤ ስሙም የሠ​ራ​ዊት ጌታ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ነው።