የያ​ዕ​ቆብ መል​እ​ክት 5:7-20

የያ​ዕ​ቆብ መል​እ​ክት 5:7-20 አማ2000

እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ። እነሆ ገበሬው የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ እስኪቀበል ድረስ እርሱን እየታገሠ የከበረውን የመሬት ፍሬ ይጠብቃል። እናንተ ደግሞ ታገሡ፤ ልባችሁንም አጽኑ፤ የጌታ መምጣት ቀርቦአልና። ወንድሞች ሆይ! እንዳይፈረድባችሁ እርስ በርሳችሁ አታጉረምርሙ፤ እነሆ ፈራጅ በደጅ ፊት ቆሞአል። ወንድሞች ሆይ! የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፤ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና። ከሁሉም በፊት ወንድሞቼ ሆይ! በሰማይም ቢሆን በምድርም ቢሆን በሌላ መሐላም ቢሆን በምንም አትማሉ፤ ነገር ግን ከፍርድ በታች እንዳትወድቁ ነገራችሁ አዎን ቢሆን አዎን ይሁን፤ አይደለምም ቢሆን አይደለም ይሁን። ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር። ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት። የእምነትም ጸሎት ድውዩን ያድናል፤ ጌታም ያስነሣዋል፤ ኀጢአትንም ሠርቶ እንደ ሆነ ይሰረይለታል። እርስ በርሳችሁ በኀጢአታችሁ ተናዘዙ። ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለ ሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኀይል ታደርጋለች። ኤልያስ እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበረ፤ ዝናብም እንዳይዘንብ አጥብቆ ጸለየ፤ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አልዘነበም፤ ሁለተኛም ጸለየ፤ ሰማዩም ዝናብን ሰጠ፤ ምድሪቱም ፍሬዋን አበቀለች። ወንድሞች ሆይ! ከእናንተ ማንም ከእውነት ቢስት አንዱም ቢመልሰው፥ ኀጢአተኛን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ነፍሱን ከሞት እንዲያድን፥ የኀጢአትንም ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ።