ትን​ቢተ ሆሴዕ 8:1-13

ትን​ቢተ ሆሴዕ 8:1-13 አማ2000

በብ​ብ​ታ​ቸው እንደ መሬት፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቤት እንደ ንስር ይመ​ጣል። ቃል ኪዳ​ኔን ተላ​ል​ፈ​ዋ​ልና፥ በሕ​ጌም ላይ ዐም​ፀ​ዋ​ልና። አም​ላክ ሆይ! እኛ እስ​ራ​ኤል ዐወ​ቅ​ንህ ብለው ወደ እኔ ይጮ​ኻሉ። እስ​ራ​ኤል ደግ​ነ​ቱን ጥሎ​አ​ልና፤ ጠላ​ትም ያሳ​ድ​ደ​ዋ​ልና። ራሳ​ቸ​ውን አነ​ገሡ፤ ከእ​ኔም ዘንድ አይ​ደ​ለም፤ አለ​ቆ​ች​ንም አደ​ረጉ፤ እኔም አላ​ወ​ቅ​ሁም፤ ለጥ​ፋ​ታ​ቸ​ውም ከብ​ራ​ቸ​ውና ከወ​ር​ቃ​ቸው ጣዖ​ታ​ትን ለራ​ሳ​ቸው አደ​ረጉ። ሰማ​ርያ ሆይ! እም​ቦ​ሳ​ሽን መልሺ፤ ቍጣ​ዬም በላ​ያ​ቸው ነድ​ዶ​አል፤ እስከ መቼም ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይ​ች​ሉም። ይህ ደግሞ በእ​ስ​ራ​ኤል ዘንድ ነው፤ ሠራ​ተኛ ሠራው፤ እር​ሱም አም​ላክ አይ​ደ​ለም፤ ሰማ​ርያ ሆይ! እን​ቦ​ሳሽ ተቅ​በ​ዝ​ብ​ዞ​አ​ልና። ነፋ​ስን ዘር​ተ​ዋ​ልና ዐውሎ ነፋ​ስን አጨዱ፤ ለነ​ዶ​አ​ቸ​ውም ኀይል የለ​ውም፤ ከፍ​ሬ​ውም ዱቄት አይ​ገ​ኝም፤ ቢገ​ኝም ጠላት ይበ​ላ​ዋል። እስ​ራ​ኤል ተው​ጦ​አል፤ በአ​ሕ​ዛ​ብም መካ​ከል ዛሬ እንደ ግትቻ ዕቃ ሆኖ​አል። ለብ​ቻ​ውም እን​ደ​ሚ​ቀ​መጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥ​ተ​ዋል፤ ኤፍ​ሬ​ምም እንደ ገና ለመ​ለመ፤ እጅ መን​ሻ​ንም ወደደ። ስለ​ዚህ ለአ​ሕ​ዛብ አል​ፈው ይሰ​ጣሉ፤ እኔም አሁን እቀ​በ​ላ​ቸ​ዋ​ለሁ፤ ንጉ​ሥ​ንና አለ​ቆ​ች​ንም ይቀቡ ዘንድ ፈጽ​መው ያን​ሣሉ። ኤፍ​ሬም መሠ​ዊ​ያን አብ​ዝ​ቶ​አ​ልና የወ​ደ​ደው መሠ​ዊያ ለኀ​ጢ​አት ሆነ​በት። ብዙ ሕጎ​ችን እጽ​ፍ​ለ​ታ​ለሁ፤ ነገር ግን ሥር​ዐ​ቱና የተ​ወ​ደ​ደው መሠ​ዊ​ያው እንደ እን​ግዳ ነገር ተቈ​ጠሩ። መሥ​ዋ​ዕ​ት​ንም ቢሠዉ፥ ሥጋ​ንም ቢበሉ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አይ​ቀ​በ​ላ​ቸ​ውም፤ አሁ​ንም በደ​ላ​ቸ​ውን ያስ​ባል፤ በኀ​ጢ​አ​ታ​ቸ​ውም ይበ​ቀ​ላ​ቸ​ዋል፤ እነ​ር​ሱም ወደ ግብፅ ይመ​ለ​ሳሉ፤ በአ​ሦ​ርም ርኩስ ነገ​ርን ይበ​ላሉ።