እግዚአብሔርም አለው፥ “ቃየል! ምን አደረግህ? የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ። ምድርንም ባረስህ ጊዜ እንግዲህ ኀይልዋን አትሰጥህም፤ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ።” ቃየልም እግዚአብሔርን አለው፥ “ኀጢአቴ ይቅር የማትባል ታላቅ ናትን? እነሆ፥ ዛሬ ከምድር ፊት ከአሳደድኸኝ፥ ከፊትህ እሰወራለሁ፤ በምድርም ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” እግዚአብሔርም አለው፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ ቃየልን የገደለ ሁሉ ሰባት እጥፍ ይበቀልበታል።” እግዚአብሔርም ቃየልን ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው ምልክት አደረገለት። ቃየልም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ፤ በኤዶም አንጻር ባለችው ኖድ በምትባለው ምድርም ኖረ። ቃየልም ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነስችም፤ ሄኖሕንም ወለደች። ከተማም ሠራ፤ የከተማይቱንም ስም በልጁ ስም “ሄኖሕ” አላት። ሄኖሕም ጋይዳድን ወለደ፤ ጋይዳድም ሜኤልን ወለደ፤ ሜኤልም ማቱሳኤልን ወለደ፤ ማቱሳኤልም ላሜሕን ወለደ። ላሜሕም ለራሱ ሁለት ሚስቶችን አገባ፤ የአንዲቱ ስም ዓዳ፥ የሁለተኛይቱ ስም ሴላ ነበር። ዓዳም ዮቤልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን የሚቀመጡት የዘላኖች አባት ነበረ። የወንድሙም ስም ኢዮቤል ነበር፤ እርሱም በገናንና መሰንቆን አስተማረ። ሴላም ደግሞ ቶቤልን ወለደች። እርሱም ናስና ብረትን የሚሠራ ሆነ። የእኅቱም ስም ኖሄም ነበረ። ላሜሕም ለሚስቶቹ ለዓዳና ለሴላ አላቸው፥ “እናንት የላሜሕ ሚስቶች ቃሌን ስሙ፤ ነገሬንም አድምጡ፤ እኔ ጐልማሳውን ስለ መቍሰሌ፤ ብላቴናውንም ስለ መወጋቴ ገድየዋለሁና፤ ቃየልን ሰባት እጥፍ ይበቀሉታል፤ ላሜሕን ግን ሰባ ጊዜ ሰባት።” አዳምም ዳግመኛ ሚስቱን ዐወቃት፤ ፀነሰችም፤ ወንድ ልጅንም ወለደች። ስሙንም ቃየል በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ሌላ ዘር ተክቶልኛል ስትል ሴት አለችው። ሴትም ወንድ ልጅ ወለደ። ስሙንም ሄኖስ አለው፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ስም መጥራት የጀመረ ነው።
ኦሪት ዘፍጥረት 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 4:10-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች