ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ እንዲህም አለው፥ “አብርሃም! አብርሃም ሆይ፥” እርሱም፥ “እነሆ፥ አለሁ” አለ። “የምትወድደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ከፍተኛው ተራራ ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፤ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሐቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ዕንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ፤ በሦስተኛውም ቀን ደረሰ። አብርሃምም ዐይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ። አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው፥ “አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቈዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን።” አብርሃምም የመሥዋዕቱን ዕንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋዉን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው፥ “አባቴ ሆይ፥” አለ፤ እርሱም፥ “ልጄ፥ ምንድን ነው?” አለው። “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?” አለው። አብርሃምም፥ “ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። እግዚአብሔር ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ ዕንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያዉ በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ።
ኦሪት ዘፍጥረት 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 22:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች