ኦሪት ዘፍጥረት 18:4-15
ኦሪት ዘፍጥረት 18:4-15 አማ2000
ውኃ እናምጣላችሁ፤ እግራችሁንም እንጠባችሁ። ከዛፉም ሥር ዕረፉ፤ እንጀራም እናምጣላችሁና ብሉ፤ ከዚያም በባሪያችሁ ዘንድ ከአረፋችሁ በኋላ፥ ወደ ዐሰባችሁት ትሄዳላችሁ።” እነርሱም፥ “እንዳልህ እንዲሁ አድርግ” አሉት። አብርሃምም ወደ ድንኳን ወደ ሚስቱ ወደ ሣራ ፈጥኖ ገባና፥ “ሦስት መስፈሪያ የተሰለቀ ዱቄት ፈጥነሽ ለውሺ፤ እንጎቻም አድርጊ” አላት። አብርሃምም ወደ ላሞቹ ሮጠ፤ እጅግ የሰባም ታናሽ ጥጃ ያዘና ለብላቴናው ሰጠው፤ ያዘጋጅም ዘንድ ተቻኮለ። እርጎና መዓር፥ ያን ያዘጋጀውንም ጥጃ አመጣ፤ በፊታቸውም አቀረበው፤ እርሱም ከዛፉ በታች በፊታቸው ቆሞ ያሳልፍላቸው ነበር፤ እነርሱም በሉ። እርሱም፥ “ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?” አለው። እርሱም፥ “በድንኳኑ ውስጥ ናት” አለው። እርሱም፥ “የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ወደ አንተ ተመልሼ እመጣለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች” አለ። ሣራም በድንኳኑ ደጃፍ በስተኋላው ቆማ ሳለች ይህን ሰማች። አብርሃምና ሣራም በዕድሜያቸው ሸምግለው ፈጽመው አርጅተው ነበር፤ በሴቶች የሚሆነውም ልማድ ከሣራ ተቋርጦ ነበር። ሣራም ለብቻዋ በልብዋ እንዲህ ስትል ሳቀች፥ “እስከ ዛሬ ገና ነኝን? ጌታዬም ፈጽሞ ሽምግሎአል።” እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ “ሣራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት? እስከ ዛሬ ገና ነኝን? በእውነትስ እወልዳለሁን? ጌታዬም አርጅትዋል እነሆ፥ እኔም አርጅቻለሁ ብላለችና። በውኑ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር አለን? የዛሬ ዓመት እንደ ዛሬው ጊዜ ወደ አንተ እመለሳለሁ፤ ሣራም ልጅን ታገኛለች።” ሣራም ስለ ፈራች “አልሳቅሁም” ብላ ካደች። እርሱም፥ “አይደለም፥ ሳቅሽ እንጂ” አላት።

