በሰናዖር ንጉሥ በአሚሮፌል፥ በእላሳር ንጉሥ በአርዮክ፥ በኤላም ንጉሥ በኮሎዶጎሞር፥ በአሕዛብ ንጉሥ በቴሮጋል ዘመን እንዲህ ሆነ፤ ከሰዶም ንጉሥ ከባላ፥ ከገሞራ ንጉሥ ከበርሳ፥ ከአዳማ ንጉሥ ከሰናአር፥ ከሲባዮ ንጉሥ ከሲምቦር፤ ሴጎር ከተባለች ከባላ ንጉሥም ጋር ጦርነት አደረጉ። እነዚህ ሁሉ በኤሌቄን ሸለቆ ተሰብስበው ተባበሩ፤ ይኸውም የጨው ባሕር ነው። ዐሥራ ሁለት ዓመት ለኮሎዶጎሞር ተገዙ፤ በዐሥራ ሦስተኛውም ዓመት ዐመፁ። በዐሥራ አራተኛውም ዓመት ኮሎዶጎሞርና ከእርሱ ጋር የነበሩት ነገሥታት መጡ፤ ረዐይትን በአስጣሮት ቃርናይም፥ ከእነርሱም ጋር ጽኑዓን ሰዎችንና ኦሚዎስን በሴዊ ከተማ ገደሉአቸው፤ በሴይር ተራራዎች ያሉ የኬሬዎስ ሰዎችንም በበረሃ አጠገብ እስከ አለችው እስከ ፋራን ዛፍ ድረስ መቱአቸው። ተመልሰውም ቃዴስ ወደ ተባለች ወደ ፍርድ ምንጭ መጡ፤ የአማሌቅን አለቆች ሁሉና በአሳሶን ታማር የሚኖሩ አሞራውያንንም ገደሉአቸው። የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥ፥ የአዳማ ንጉሥና የሲባዮን ንጉሥ፥ ሴጎር የተባለች የባላቅ ንጉሥም ወጡ፤ እነዚህ ሁሉ በጨው ሸለቆ በእነርሱ ላይ ለሰልፍ ወጡ፤ ከኤላም ንጉሥ ከኮሎዶጎሞር፥ ከአሕዛብ ንጉሥ ከቴሮጋል፥ ከሰናዖር ንጉሥ ከአሜሮፌል፥ ከእላሳር ንጉሥ ከአርዮክ ጋር ተጋጠሙ። እነዚህ አራቱ ነገሥታት ከአምስቱ ነገሥታት ጋር ተዋጉ። ያም የጨው ሸለቆ የዝፍት ጕድጓዶች ነበሩበት። የሰዶም ንጉሥና የገሞራ ንጉሥም ሸሹና በዚያ ወደቁ፤ የቀሩትም ወደ ተራራማው ሀገር ሸሹ። የሰዶምንና የገሞራን ፈረሶች ሁሉ፥ ስንቃቸውንም ሁሉ ይዘው ሄዱ። እነርሱም የአብራምን የወንድም ልጅ ሎጥንና ገንዘቡን ይዘው ሄዱ። እርሱ በሰዶም ይኖር ነበርና። ከአመለጡትም አንድ ሰው መጣ፤ ለዕብራዊው ለአብራምም ነገረው፤ እርሱም የኤስኮል ወንድምና የአውናን ወንድም በሆነ በአሞራዊው የመምሬ ዛፍ ይኖር ነበር፤ እነዚያም ከአብራም ጋር ቃል ኪዳን ገብተው ነበር። አብራምም የወንድሙ ልጅ ሎጥ እንደ ተማረከ በሰማ ጊዜ ወገኖቹንና ቤተሰቦቹን ሁሉ ቈጠራቸው፤ እነርሱም ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሆኑ፤ እስከ ዳን ድረስ ተከትሎ አሳደዳቸው። እርሱም ከብላቴኖቹ ጋር በሌሊት ደረሰባቸው፤ መታቸውም፤ በደማስቆ ግራ እስካለችውም እስከ ሖባ ድረስ አሳደዳቸው። የሰዶምን ፈረሶች ሁሉ አስመለሰ፤ ደግሞም የወንድሙን ልጅ ሎጥንና ንብረቱን፥ ሴቶችንና ሕዝቡንም አስመለሰ።
ኦሪት ዘፍጥረት 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 14:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች