የእግዚአብሔርም እጅ በላዬ ነበረ፤ እግዚአብሔርም በመንፈሱ አወጣኝ፤ አጥንቶችም በሞሉበት ሸለቆ መካከል አኖረኝ። በእነርሱም አንጻር በዙሪያቸው አዞረኝ፤ እነሆም በሜዳው እጅግ ነበሩ፤ እነሆም እጅግ ደርቀው ነበር። እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ አጥንቶች በሕይወት ይኖራሉን?” አለኝ። እኔም፥ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ታውቃለህ” አልሁ። እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “በእነዚህ አጥንቶች ላይ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፦ እናንተ የደረቃችሁ አጥንቶች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ አጥንቶች እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእናንተ ላይ የሕይወትን መንፈስ አመጣለሁ። ጅማትንም እሰጣችኋለሁ፤ ሥጋንም አወጣባችኋለሁ፤ በእናንተም ላይ ቍርበትን እዘረጋለሁ፤ ትንፋሽንም አገባባችኋለሁ፤ በሕይወትም ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።” እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ስናገርም ድምፅ ሆነ፤ እነሆም መናወጥ ሆነ፤ አጥንቶችንም እየራሱ በሆነ በሰውነቱ ከአጥንቶች ጋር አንድ አደረጋቸው። እኔም አየሁ፤ እነሆም ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም ወጣ፤ ቍርበትም በላያቸው ተዘረጋ፤ ትንፋሽ ግን አልነበረባቸውም። እርሱም፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስ ትንቢት ተናገር፤ ለነፋስም፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፋስ ሆይ! ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ እነዚህ ሙታን በሕይወት ይኖሩ ዘንድ እፍ በልባቸው በል” አለኝ። እንዳዘዘኝም ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንፋሽም ገባባቸው፤ ሕያዋንም ሆኑ፤ እጅግም ታላቅ ሠራዊት ሆነው በእግራቸው ቆሙ።
ትንቢተ ሕዝቅኤል 37 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ሕዝቅኤል 37:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች