ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ገብተው እንዲህ አሉት፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በምድረ በዳ በዓል ያደርግልኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።’ ” ፈርዖንም፥ “የእስራኤልን ልጆች እለቅቅ ዘንድ ቃሉን የምሰማው እርሱ እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም ደግሞ አልለቅቅም” አለ። እነርሱም፥ “ቸነፈር ወይም ሰይፍ እንዳይጥልብን የሦስት ቀን መንገድ በምድረ በዳ እንድንሄድ፥ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እንድንሠዋ የዕብራውያን አምላክ ጠራን” አሉት። የግብፅ ንጉሥም፥ “እናንተ ሙሴና አሮን፥ ሕዝቡን ለምን ሥራቸዉን ታስተዋላችሁ? ወደ ተግባራችሁ ሂዱ” አላቸው። ፈርዖንም ለሕዝቡ አለ፥ “እነሆ፥ ሕዝቡ በምድር በጣም በዝተዋል፤ እናንተም ከሥራቸው አሳርፋችኋቸዋል። ፈርዖንም በዚያ ቀን የሕዝቡን አሠሪዎችና ጸሓፊዎች እንዲህ ሲል አዘዘ፦ “እንደ ወትሮው ለጡብ ሥራ ደግሞ ገለባ ለሕዝቡ አትስጡ፤ ነገር ግን እነርሱ ሄደው ለራሳቸው ገለባ ይሰብስቡ። ቀድሞ ያደርጉት የነበረውን የጡብ ቍጥር እንዲሁ በየቀኑ በእነርሱ ላይ አድርጉት፤ ምንም ከእርሱ አታጕድሉ፤ ሥራ ሰልችተዋልና ስለዚህ፦ ‘ለአምላካችን እንድንሠዋ እንሂድ’ እያሉ ይጮሃሉ። በእነዚህ ሰዎች ላይ ሥራው ይክበድባቸው፤ ይህን ብቻ ያስባሉ፤ ከንቱ ቃልም አያስቡም።” የሕዝቡም አሠሪዎችና ጸሓፊዎች ወጡ፤ ሕዝቡንም፥ “ፈርዖን እንዲህ ይላል፦ እንግዲህ ገለባ አይሰጣችሁም፤ እናንተ ሂዱ፤ ከምታገኙበትም ስፍራ ገለባ ሰብስቡ፤ ከምትሠሩት ጡብ ግን ምንም አይጐድልም” አሉአቸው። ሕዝቡም ሁሉ ስለ ገለባ እብቅ ሊሰበስቡ በግብፅ ምድር ሁሉ ተበተኑ። አሠሪዎቹም፥ “ገለባ ትቀበሉበት እንደነበረ ጊዜ የቀን ሥራችሁን ጨርሱ” እያሉ ያስቸኩሉአቸው ነበር። የፈርዖንም ሹሞች፥ “ቀድሞ ታደርጉት እንደ ነበራችሁ እንደ ትናንትናውና እንደ ትናንትና በስቲያው የተቈጠረውን ጡብ ዛሬስ ስለምን አትጨርሱም?” እያሉ በእስራኤል ልጆች ላይ የተሾሙትን አለቆች ይገርፉ ነበር። የእስራኤል ልጆች አለቆችም ወደ ፈርዖን ገቡ፥ “ለምን በአገልጋዮችህ እንዲህ ታደርጋለህ? ገለባ አይሰጡአቸውም፤ ጡቡንም ሥሩ ይሉአቸዋል፤ እነሆም፥ አገልጋዮችህ ይገረፋሉ፤ ይገፋሉም፤ ግፉም በአንተ ሕዝብ ላይ ነው” ብለው ጮኹ። እርሱ ግን፥ “እናንተ አርፋችኋል፤ ቦዝናችኋል፤ ስለዚህም፦ ‘እንሂድ ለእግዚአብሔርም እንሠዋ’ ትላላችሁ። አሁንም ሂዱ፤ ሥሩ፤ ገለባም አይሰጡአችሁም፤ የጡቡን ቍጥር ግን ታመጣላችሁ” አላቸው። የእስራኤልም ልጆች አለቆች ዕለት ዕለት ከምትሠሩት ከጡቡ ቍጥር ምንም አታጕድሉ ባሉአቸው ጊዜ ነገሩ እንደ ከፋባቸው አዩ። ከፈርዖንም ዘንድ ሲወጡ ሙሴንና አሮንን በፊታቸው ቆመው ተገናኙአቸው። እነርሱም፥ “በፈርዖንና በሹሞቹ ፊት ሽታችንን አግምታችሁታልና፥ ይገድለንም ዘንድ ሰይፍን በእጁ ሰጥታችሁታልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ፤ ይፍረድባችሁም” አሉአቸው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመለሰና፥ “ጌታ ሆይ፥ ስለምን ይህን ሕዝብ አስከፋህ? ስለ ምንስ ላክኸኝ?
ኦሪት ዘፀአት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 5:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች