ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ አላቸው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤ ከእናንተ ዘንድ ለእግዚአብሔር ቍርባንን አቅርቡ፤ የልብ ፈቃድ ያለው ከገንዘቡ የመጀመሪያውን ለእግዚአብሔር ያምጣ፤ ወርቅና ብር፥ ናስም፤ ሰማያዊም፥ ሐምራዊም፥ ድርብ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፤ ቀይ ቀለምም የገባበት የአውራ በግ ቍርበት፥ የአቆስጣም ቍርበት፥ የማይነቅዝም ዕንጨት፤ ለመብራትም ዘይት፥ ለቅብዐት ሽቱን፥ ለማዕጠንት ዕጣንን፤ የመረግድ ድንጋይና የተቀረጸ ድንጋይ፥ ለልብሰ መትከፍና ለልብሰ እንግድዓ የሚደረግ ፈርጥ ያምጣ። “በእናንተ ዘንድ ያለ፥ በልቡ ጥበበኛ የሆነ ሁሉ መጥቶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ያድርግ። ድንኳኑንም፥ አደባባዩንም፥ መደረቢያውንም፥ መያዣዎቹንም፥ ሳንቆቹንም፥ መወርወሪያዎቹንም፥ ምሰሶዎችንና እግሮቻቸውን፤ የቃል ኪዳኑን ታቦትም፥ መሎጊያዎቹንም፥ የስርየት መክደኛውንም፥ መጋረጃውንም፤ ገበታውንና መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ኅብስተ ገጹንም፤ መብራት የሚያበሩበትን መቅረዙን፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ ቀንዲሉንም፥ የመብራቱንም ዘይት፤ የዕጣኑንም መሠዊያ፥ መሎጊያዎቹንም፥ የቅብዐቱንም ዘይት፥ ጣፋጩንም ዕጣን፥ ለማደሪያውም ደጃፍ የሚሆን የደጃፉን መጋረጃ፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያውን፥ የናሱንም መከታ፥ መሎጊያዎቹንም፥ ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንም፥ መቀመጫውንም፤ የአደባባዩን መጋረጆች፥ ምሰሶዎችንም፥ እግሮቻቸውንም፥ የአደባባዩንም ደጃፍ መጋረጃ፤ የማደሪያውን ካስማዎች፥ የአደባባዩንም ካስማዎች፥ አውታሮቻቸውንም፤ በመቅደስ ውስጥ ለማገልገል በብልሃት የተሠሩትን ልብሶች፥ በክህነት ያገለግሉበት ዘንድ የተቀደሱትን የካህኑን የአሮንን ልብሶች፥ የልጆቹንም ልብሶች።” የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ከሙሴ ዘንድ ወጡ። ከእነርሱም ሰው ሁሉ እያንዳንዱ ልቡ እንዳነሣሣው፥ መንፈሱም እሺ እንዳሰኘው ለምስክሩ ድንኳን ሥራ ለማገልገያውም ሁሉ ለመቅደስ ልብስ ለእግዚአብሔር ስጦታ አመጡ። ወንዶችና ሴቶችም ልባቸው እንደ ፈቀደ ማርዳዎችን፥ ሎቲዎችንም፥ ቀለበቶችንም፥ ድሪዎችንም፥ የወርቅ ጌጦችንም ሁሉ አመጡ፤ ሰዎችም ሁሉ የወርቅ ስጦታ ለእግዚአብሔር አቀረቡ። ሰማያዊም፥ ሐምራዊም፥ ቀይ ግምጃም፥ የተፈተለ በፍታም፥ የፍየል ጠጕርም፥ ቀይ የአውራ በግ ቍርበትም፥ የአቆስጣ ቍርበትም ያላቸው ሰዎች ሁሉ አመጡ። ስዕለት የተሳለ ሁሉ፥ የብርንም፥ የናስንም ስጦታ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቀረበ፤ የማይነቅዝ ዕንጨት ያለው ሁሉ ለድንኳኑ ማገልገያ ለሚያስፈልገው ሥራ አመጣ። በልባቸው ጥበበኞች የሆኑ ሴቶችም በእጃቸው ፈተሉ፤ የፈተሉትንም ሰማያዊውን፥ ሐምራዊውንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ጥሩውንም በፍታ አመጡ። ልባቸውም በጥበብ ያስነሣቸው ሴቶች ሁሉ የፍየልን ጠጕር ፈተሉ። አለቆችም የመረግድ ድንጋይና የተቀረጸ ድንጋይን ለልብሰ መትከፍና ለልብሰ እንግድዓ የሚገቡትንም ፈርጦችን፥ ለመብራትም፥ ለቅብዐት ዘይትም፥ ለጣፋጭ ዕጣንም ሽቱንና ዘይትን አመጡ። ከእስራኤል ልጆችም ያመጡ ዘንድ ልባቸው ያስነሣቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉ ሙሴ ይሠራ ዘንድ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር ስጦታ በፈቃዳቸው አመጡ።
ኦሪት ዘፀአት 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 35:4-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች