እኔ በልቤ፥ “ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ እነሆ፥ መልካምንም እይ” አልሁ፤ ይህም እነሆ፥ ከንቱ ነበረ። ሣቅን፥ “ሽንገላ ነህ፤ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ?” አልሁት። የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች የሚሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ደስ ለማሰኘት፥ ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። እኔ ሥራዬን አበዛሁ፥ ቤቶችንም ለእኔ ሠራሁ፥ ወይንም ተከልሁ። የወይንና የአትክልት ቦታን አደረግሁ፥ ወይንና ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው። የሚያፈራ እንጨትንና የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያን አደረግሁ። ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ገዛሁ፤ በቤት የተወለዱ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን፥ የከበረውንም የነገሥታትንና የአውራጆችን መዝገብ ለራሴ ሰበሰብሁ፤ ሴቶችና ወንዶች አዝማሪዎችን፥ የሰዎች ልጆችንም ተድላ አደረግሁ፤ የወይን ጠጅ ጠማቂዎችንና አሳላፊዎችንም አበዛሁ። ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ታላቅም ሆንሁ። ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸናችልኝ። ዐይኖቼ ከፈለጉት ሁሉ አላጣሁም፥ ልቤንም ከደስታ ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ልቤ በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ ዕድል ፋንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ፥ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን፥ ሽንገላንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ ፥ ምክርን የሚከተል፥ ምሳሌንስ ሁሉ የሚያደርግላት ሰው ማን ነው? እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ከአላዋቂ ይልቅ ለብልህ ብልጫ እንዳለው ተመለከትሁ። የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸውና፤ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፥ “አላዋቂን የሚያገኘው እንዲሁ እኔንም ያገኘኛል፤ እኔም ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ?” አልሁ፤ የዚያን ጊዜም በልቤ፥ “ይህ ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ፥ አላዋቂ በከንቱ መናገርን ያበዛልና። ለብልህ ከአላዋቂ ጋር ለዘለዓለም መታሰቢያ የለውም፤ እነሆ፥ ዘመን ይመጣልና ሁሉም ይረሳል፤ ብልህስ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል?
መጽሐፈ መክብብ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መክብብ 2:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች