“አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት ወደምትገባባት ምድር ባመጣህ ጊዜ፥ ከፊትህም ብዙና ታላላቅ አሕዛብን፥ ከአንተ የበለጡትን፥ የበረቱትንም ሰባቱን አሕዛብ፥ ኬጤዎናዊውን፥ ጌርጌሴዎናዊውንም፥ አሞሬዎናዊውንም፥ ከነዓናዊውንም፥ ፌርዜዎናዊውንም፥ ኤዌዎናዊውንም፥ ኢያቡሴዎናዊውንም ባወጣ ጊዜ፥ አምላክህ እግዚአብሔርም በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸውና በመታሃቸው ጊዜ፥ ፈጽመህ አጥፋቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አታድርግ፤ አትማራቸውም፤ ከእነርሱም ጋር አትጋባ፤ ሴት ልጅህን ለወንድ ልጁ አትስጥ፥ ሴት ልጁንም ለወንድ ልጅህ አትውሰድ። ልጅህን ከእኔ ያርቀዋልና፤ ሌሎችን አማልክትም ያመልካልና። የእግዚአብሔርም ቍጣ ይነድድባችኋል፤ ፈጥኖም ያጠፋችኋል። ነገር ግን እንዲህ አድርጉባቸው፤ መሠዊያቸውን አፍርሱ፤ ሐውልቶቻቸውንም ሰባብሩ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቻቸውንም ቍረጡ፥ የአማልክቶቻቸውንም ምስል በእሳት አቃጥሉ። “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር አንተ ቅዱስ ሕዝብ ነህና፤ በምድር ፊት ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ ይልቅ ለእርሱ ለራሱ ሕዝብ ትሆንለት ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦሃልና። እግዚአብሔርም የወደዳችሁና የመረጣችሁ፥ ከአሕዛብ ሁሉ ስለ በዛችሁ አይደለም፤ እናንት ከአሕዛብ ሁሉ ጥቂቶች ነበራችሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ ወደዳችሁ፥ ለአባቶቻችሁም የማለላቸውን መሐላ ስለ ጠበቀ፥ ስለዚህ እግዚአብሔር በጽኑ እጅ፥ በተዘረጋችም ክንድ አወጣችሁ፤ ከባርነትም ቤት ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ አዳናችሁ። አንተም አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ አምላክ እንደ ሆነ፥ ለሚወድዱትም፥ ትእዛዙንም ለሚጠብቁ ቃል ኪዳኑንና ምሕረቱን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ የታመነ አምላክ እንደ ሆነ ዕወቅ፤ የሚጠሉትን ለማጥፋት በፊታቸው ብድራት ይመልስባቸዋል፤ ለሚጠላው አይዘገይም፤ ነገር ግን በፊቱ ብድራትን ይመልስበታል። እንግዲህ ታደርጓት ዘንድ እኔ ዛሬ ለእናንተ የማዝዛትን ትእዛዝና ሥርዐት፥ ፍርድንም ጠብቁ። “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምታችሁ ብትጠብቋት፥ ብታደርጓትም፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለእናንተ ይጠብቅላችኋል፤ ይወድድህማል፤ ይባርክህማል፤ ያባዛህማል፤ ይሰጥህም ዘንድ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር የሆድህን ፍሬ፥ የመሬትህንም ፍሬ፥ እህልህን፥ ወይንህንም፥ ዘይትህንም፥ የከብትህንም ብዛት፥ የበግህንም መንጋ ይባርክልሃል። ከአሕዛብም ሁሉ ይልቅ የተባረክህ ትሆናለህ፤ ከሴቶችህ መካን አትኖርም፤ ልጆች የሌሏት አገልጋይም አትኖርም፤ ከከብትህም መካን አይኖርም። በግብፃውያን ላይ ሲመጣ ያየኸውን ክፉ ሕማምና ደዌ ሁሉ እግዚአብሔር ከአንተ ያርቅልሃል፤ ያየኸውንም መከራ ሁሉ ወደ አንተ አያመጣውም፤ ከአንተም በሚጠሉህ ሁሉ ላይ ይመልሰዋል። አምላክህም እግዚአብሔር የሚሰጥህን የአሕዛብ ምርኮ ትበላለህ፤ ዐይንህም አታዝንላቸውም፤ ያም ለአንተ ክፉ ይሆንብሃልና አማልክቶቻቸውን አታምልካቸው። “በልብህም፦ እነዚህ አሕዛብ ከእኔ ይልቅ ይበዛሉና አወጣቸው ዘንድ እንዴት እችላለሁ? ብለህ፥ አትፍራቸው፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በፈርዖንና በግብፃውያን ሁሉ ያደረገውን ፈጽመህ አስብ፤ አምላክህ እግዚአብሔር ዓይንህ እያየች፥ ታላቅ መቅሠፍትን፥ ምልክትንም፥ ተአምራትንም፥ የጸናችውንም እጅ፥ የተዘረጋውንም ክንድ አድርጎ እንዳወጣህ፤ እንዲሁ አምላክህ እግዚአብሔር አንተ በምትፈራቸው በአሕዛብ ሁሉ ላይ ያደርጋል። ደግሞም አምላክህ እግዚአብሔር የቀሩት፥ ከፊትህም የተሸሸጉት እስኪጠፉ ድረስ መቅሠፍትን ይልክባቸዋል። ከፊታቸው አትደንግጥ፤ አምላክህ እግዚአብሔር፥ ከአንተ ጋር ነውና፥ እርሱም አምላክህ እግዚአብሔር ታላቅና ጽኑዕ ነውና። አምላክህም እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ በጥቂት በጥቂቱ ከፊትህ ያጠፋቸዋል፤ ምድርም ምድረ በዳ እንዳትሆን የምድረ በዳ አራዊትም እንዳይበዙብህ ፈጥኜ አጠፋቸዋለሁ አትበል። አምላክህ እግዚአብሔር ግን እነርሱን በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፥ እስኪጠፉም ድረስ በታላቅ ውርደት ይደመስሳቸዋል። ነገሥታቶቻቸውንም በእጅህ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ ስማቸውንም ከዚያ ቦታ ያጠፋል፤ እስክታጠፋቸው ድረስ ማንም ከፊትህ ይቆም ዘንድ አይችልም። የአምላኮቻቸውን ምስል በእሳት ታቃጥላለህ፤ ከእነርሱም የተሠራባቸውን ብርንና ወርቅን፥ አትመኝ፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና እንዳትበድልበት ከእርሱ ምንም አትውሰድ። ርኩስን ነገር ወደ ቤትህ አታግባ፤ እንደ እርሱም ርጉም ትሆናለህ፤ ርጉም ነውና መጸየፍን ተጸየፈው፤ መጥላትንም ጥላው።
ኦሪት ዘዳግም 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘዳግም 7:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች