እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የኤዶምያስን ንጉሥ አጥንት አመድ እስኪሆን ድረስ አቃጥሎታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የሞዓብ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በሞዓብ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የከተሞችዋንም መሠረቶች ትበላለች፤ ሞዓብም በድካምና በውካታ፥ በመለከትም ድምፅ ይሞታል፤ ፈራጅንም ከመካከልዋ አጠፋለሁ፤ ከእርሱም ጋር አለቆችዋን ሁሉ እገድላለሁ” ይላል እግዚአብሔር። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የእግዚአብሔርን ሕግ አፍርሰዋልና፥ ትእዛዙንም አልጠበቁምና፥ አባቶቻቸውም የተከተሉት ከንቱ ነገር አስቶአቸዋልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የይሁዳ ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። በይሁዳ ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ የኢየሩሳሌምንም መሠረቶች ትበላለች።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ጻድቁን በብር፥ ችጋረኛውንም ምድርን በሚረግጡበት አንድ ጥንድ ጫማ ሸጠውታልና ስለ ሦስት ወይም ስለ አራት የእስራኤል ኀጢአት መቅሠፍቴን ከማድረግ አልመለስላቸውም። የድሆችን ራስ ይቀጠቅጣሉ፤ የትሑታንንም ፍርድ ያጣምማሉ፤ የአምላካቸውንም ስም ያረክሱ ዘንድ አባትና ልጁ ወደ አንዲት ሴት ይገባሉ፤ ልብሳቸውንም አስረው ለመሥዊያው መጋረጃ ያደርጋሉ፤ በአምላካቸውም ቤት የቅሚያ ወይን ጠጅ ይጠጣሉ። እኔ ግን ቁመቱ እንደ ዝግባ ቁመት፥ ብርታቱም እንደ ወይራ ዛፍ የነበረውን አሞራዊውን ከፊታቸው አጠፋሁ፤ ፍሬውንም ከላዩ፥ ሥሩንም ከታቹ አጠፋሁ። የአሞራዊውንም ምድር ትወርሱ ዘንድ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤ በምድረ በዳም አርባ ዓመት መራኋችሁ። ከወንድ ልጆቻችሁም ነቢያትን፥ ከጐበዛዝቶቻችሁም ለእኔ የተለዩትን አስነሣሁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! ይህ እንደዚህ አይደለምን?” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ ግን ለእኔ የተለዩትን የወይን ጠጅ አጠጣችኋቸው፤ ነቢያቱንም፥ “ትንቢትን አትናገሩ ብላችሁ ከለከላችኋቸው። “ስለዚህ ሠረገላ ብርዑን እንዲያደቅ፥ በበታቻችሁ ባለ መሬት እኔ አደቅቃችኋለሁ። የሚሮጥ ሰው ማምለጥ አይችልም፤ ኀይለኛውም በብርታቱ አይዝም፤ አርበኛውም ነፍሱን አያድንም። ቀስተኛውም አይቆምም፤ ፈጣኑም አያመልጥም፤ ፈረሰኛውም ነፍሱን አያድንም፤ ልበ ሙሉው ኀይለኛም በኀይሉ አይተማመንም፤ ነገር ግን በዚያ ቀን ዕራቁቱን ሆኖ ይሸሻል” ይላል እግዚአብሔር።
ትንቢተ አሞጽ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 2:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች