እኛ በተወለድንበት በጳርቴ፥ በሜድ፥ በኢላሜጤ፥ በሁለቱ ወንዞች መካከል፥ በይሁዳ፥ በቀጰዶቅያ፥ በጳንጦስና በእስያ፥ በፍርግያ፥ በጵንፍልያ፥ በግብፅ፥ በሊብያ አውራጃ፥ በቀርኔን የምንኖር፥ ከሮሜም የመጣን አይሁድ፥ መጻተኞችም፥ ከቀርጤስና ከዐረብም የመጣን፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ጌትነት በየሀገራችን ቋንቋ ሲናገሩ እንሰማቸዋለን።” ሁሉም ተገረሙ፤ የሚሉትንም አጡ፥ እርስ በርሳቸውም፥ “እንጃ! ይህ ነገር ምን ይሆን?” ተባባሉ። እኩሌቶቹ ግን “እነዚህስ ጉሽ ጠጅ ጠግበው ሰክረዋል” ብለው ሳቁባቸው። ጴጥሮስም ከዐሥራ አንዱ ጋር ቆሞ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፥ “እናንተ የአይሁድ ሰዎች፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ ይህን ዕወቁ፤ ቃሌንም ስሙ። ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፤ ከቀኑ ገና ሦስተኛ ሰዓት ነውና። ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው። በኋለኛዪቱ ቀን እንዲህ ይሆናል ይላል እግዚአብሔር፦ ሥጋን በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈስሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁ ትንቢት ይናገራሉ፤ ጐልማሶቻችሁ ራእይን ያያሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ። በወንዶችና በሴቶች ባሮች ላይም ያንጊዜ መንፈሴን አፈስሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ። በላይ በሰማይ ተአምራትን፥ በታች በምድርም ምልክቶችን፥ ደምን እሳትንና ጢስንም እሰጣለሁ። የምትገለጠው ታላቅዋ የእግዚአብሔር ቀን ሳትመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ፥ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣል። የእግዚአብሔርንም ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል። “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ። እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፤ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና። ዳዊትም ስለ እርሱ እንዲህ አለ፦ እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሤት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ። ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፥ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና። የሕይወትን መንገድ አሳየኸኝ፤ ከፊትህ ጋራ ደስታን አጠገብኸኝ። “እናንተ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ አባቶች አለቃ ስለ ዳዊት ነገር እንደ ሞተ እንደ ተቀበረም፥ መቃብሩም እስከ ዛሬ ድረስ በእኛ ዘንድ እንደ አለ ገልጬ እንድነግራችሁ ትፈቅዱልኛላችሁን? ነቢይ ስለ ነበረ፥ ከአብራኩም የተገኘውን በዙፋኑ እንዲያነግሥለት እግዚአብሔር መሐላን እንደ ማለለት ስለ ዐወቀ፥ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ፥ ሥጋዉም በመቃብር እንደማይቀር፥ ጥፋትንም እንደማያይ አስቀድሞ ዐውቆ ተናገረ። እርሱን ኢየሱስን እግዚአብሔር አስነሣው፤ ለዚህም እኛ ሁላችን ምስክሮቹ ነን። አሁን ግን በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ብሎና የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ገንዘብ አድርጎ ይህን ዛሬ የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው። ዳዊት ወደ ሰማይ አልወጣም፥ ነገር ግን እርሱ አለ፦ ጌታ ጌታዬን አለው፦ በቀኜ ተቀመጥ። ጠላቶችህን ከእግርህ ጫማ በታች እስክጥላቸው ድረስ። እንግዲህ የእስራኤል ወገኖች ሁሉ እናንተ የሰቀላችሁትን ኢየሱስን እግዚአብሔር ጌታም መሢሕም እንዳደረገው በርግጥ ይወቁ።” ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተከፈተ፤ ጴጥሮስንና ወንድሞቹ ሐዋርያትንም፥ “ወንድሞቻችን ሆይ፥ ምን እናድርግ?” አሏቸው። ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፥ “ንስሓ ግቡ፤ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ ኀጢአታችሁም ይሰረይላችኋል፤ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ትቀበላላችሁ። ተስፋዉ ለእናንተና ለልጆቻችሁ፥ እግዚአብሔር አምላካችንም ለሚጠራቸው ርቀው ለነበሩ ሁሉ ነውና።” ሌላም ብዙ ነገር ነገራቸው፤ “ከዚህ ከክፉ ዓለምም ነፍሳችሁን አድኑ” ብሎ መከራቸው። ቃሉንም ተቀብለው ተጠመቁ፤ በዚችም ዕለት ሦስት ሺህ ያህል ሰዎች ተጨመሩ።
የሐዋርያት ሥራ 2 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 2
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 2:9-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች