የሶርህያ ልጅ ኢዮአብም የንጉሡ ልብ ወደ አቤሴሎም እንዳዘነበለ ዐወቀ። ኢዮአብም ወደ ቴቁሔ ልኮ ከዚያ ብልሃተኛ ሴት አስመጣና፥ “አልቅሺ፤ የኀዘንም ልብስ ልበሺ፤ ዘይትም አትቀቢ፤ ስለ ሞተ ሰውም ብዙ ዘመን እንደምታለቅስ ሴት ሁኚ፤ ወደ ንጉሡም ገብተሽ እንዲህ ያለውን ቃል ንገሪው” አላት፤ ኢዮአብም ቃሉን በእርስዋ አፍ አደረገ። እንዲሁም የቴቁሔዪቱ ሴት ወደ ንጉሥ ገብታ በግንባርዋ በምድር ላይ ወደቀች፤ ሰግዳም “ንጉሥ ሆይ፥ አድነኝ፤ አድነኝ” አለች። ንጉሡም፥ “ምን ሆነሻል?” አላት። እርስዋም አለች፥ “በእውነት እኔ ባሌ የሞተብኝ ባልቴት ሴት ነኝ። ለእኔም ለአገልጋይህ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩኝ፤ በሜዳም ተጣሉ፤ የሚገላግላቸውም አልነበረም፤ አንዱም ሌላውን መትቶ ገደለው። እነሆም፥ ዘመዶች ሁሉ በባሪያህ ላይ ተነሡ፤ ስለ ገደለው ስለ ወንድሙ ነፍስ እንገድለው ዘንድ ወንድሙን የገደለውን አውጪ አሉኝ፤ እንዲሁም ደግሞ ለባሌ ስምና ዘር በምድር ላይ እንዳይቀር ወራሹን የቀረውን መብራቴን ያጠፋሉ፤” ንጉሡም ሴቲቱን፥ “ወደ ቤትሽ በሰላም ሂጂ፤ እኔም ስለ አንቺ አዝዛለሁ” አላት። የቴቁሔዪቱም ሴት ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ኀጢአቱ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ ይሁን፤ ንጉሡና ዙፋኑ ንጹሕ ይሁን” አለችው። ንጉሡም፥ “የሚናገርሽ ማን ነው? አምጪልኝ፤ ከዚያም በኋላ ደግሞ አይነካሽም” አለ። ያችም ሴት፥ “ለመግደል ባለ ደሞች እንዳይበዙ፤ ልጄንም እንዳይገድሉብኝ ንጉሥ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ያስብ” አለች። እርሱም፥ “የልጅሽስ አንዲት የራሱ ጠጕር በምድር ላይ እንዳትወድቅ ሕያው እግዚአብሔርን” አላት። ሴቲቱም፥ “እኔ አገልጋይህ ለጌታዬ ለንጉሥ አንድ ቃል ልናገር” አለች፤ እርሱም፥ “ተናገሪ” አላት። ሴቲቱም አለች፥ “በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስለምን አሰብህ? ወይስ ንጉሥ ያሳደደውን ስላላስመለሰ እንደ በደል ከንጉሥ አፍ ይህ ቃል ወጥቶአልን? ሞትን እንሞታለንና፥ በምድርም ላይ እንደ ፈሰሰና እንደማይመለስ ውኃ እንሆናለንና፥ እግዚአብሔርም ነፍስን ይወስዳል። የተጣለውንም ከእርሱ ያርቅ ዘንድ ያስባል። አሁንም ሕዝቡ ስለሚያዩኝ ይህን ነገር ለጌታዬ ለንጉሥ እነግረው ዘንድ መጥቻለሁ፤ እኔም አገልጋይህ፦ የእኔን የአገልጋዩን ልመና ንጉሡ ያደርግልኝ እንደ ሆነ ለጌታዬ ለንጉሥ ልናገር፤ እኔንና ልጄን ከእግዚአብሔር ርስት ያርቀን ዘንድ ከሚሻ ሰው እጅ ያድን ዘንድ ንጉሡ አገልጋዩን ይሰማል አልሁ።” ያችም ሴት አለች፥ “መልካሙንና ክፉውን ነገር ለመስማት ንጉሡ ጌታዬ እንደ መሥዋዕትና እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነውና የጌታዬ የንጉሡ ቃል እንደዚሁ ነው፤ አምላክህም እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ይሁን።” ንጉሡም ለሴቲቱ መልሶ፥ “የምጠይቅሽን ነገር አትሰውሪኝ” አላት። ሴቲቱም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ይናገር” አለች። ንጉሡም፥ “በዚህ ሁሉ ነገር የኢዮአብ እጅ ከአንቺ ጋር አለን?” አላት። ሴቲቱም ንጉሡን አለችው፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ! ጌታዬ ንጉሥ ከተናገረው ነገር ሁሉ ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሊል የሚችል የለም፤ አገልጋይህ ኢዮአብ አዝዞኛል፤ ይህንም ቃል ሁሉ በአገልጋይህ አፍ አደረገው። ይህን ነገር እናገር ዘንድ እንድመጣ ይህን ምክር ያደረገ አገልጋይህ ኢዮአብ ነው። ጌታዬ ግን በዚህ ዓለም የሚደረገውን ሁሉ ታውቅ ዘንድ እንደ መልአከ እግዚአብሔር ጥበብ ጥበበኛ ነህ፤” ንጉሡም ኢዮአብን፥ “እነሆ፥ ይህን ነገር አድርጌአለሁ፤ ሂድና ብላቴናውን አቤሴሎምን መልሰው” አለው። ኢዮአብም በምድር ላይ በግንባሩ ወድቆ ሰገደለት፤ ንጉሡንም አመሰገነ፤ ኢዮአብም፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የአገልጋይህን ነገር አድርገሃልና በዐይንህ ፊት ሞገስን እንዳገኘ አገልጋይህ ዛሬ ዐወቀ” አለ። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ ጌድሶር ሄደ፤ አቤሴሎምንም ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው። ንጉሡም፥ “ወደ ቤቱ ይሂድ እንጂ ፊቴን እንዳያይ” አለ፤ አቤሴሎምም ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። በእስራኤል ሁሉ ዘንድ እንደ አቤሴሎም በውበቱ ያማረ ሰው አልነበረም፤ ከእግሩ እስከ ራሱ ድረስ ነውር አልነበረበትም። ቀድሞ በመጀመሪያ ዘመን ጠጕሩ ይከብደው ነበርና በዓመት አንድ ጊዜ ይቈረጠው ነበር፤ ሲቈረጥም የራሱ ጠጕር በንጉሥ ሚዛን ሁለት መቶ ሰቅል ያህል ይመዝን ነበር። ለአቤሴሎምም ሦስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት። የሴቲቱ ልጅም ስም ትዕማር ይባላል። ያችውም ሴት መልከ መልካም ነበረች፤ እርሷም የሰሎሞን ልጅ የሮብአም ሚስት ሆና አቢያን ወለደችለት። አቤሴሎምም በኢየሩሳሌም ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፤ የንጉሡንም ፊት አላየም። አቤሴሎምም ወደ ንጉሡ ይልከው ዘንድ ወደ ኢዮአብ ላከ፤ ወደ እርሱም ሊመጣ አልወደደም፤ ሁለተኛም ላከበት፤ ሊመጣ ግን አልወደደም። አቤሴሎምም ብላቴኖቹን፥ “በእርሻዬ አጠገብ ያለችውን የኢዮአብን እርሻ እዩ፤ በዚያም ገብስ አለው፤ ሄዳችሁ በእሳት አቃጥሉት” አላቸው። የአቤሴሎምም ብላቴኖች እርሻውን አቃጠሉት። የኢዮአብም አሽከሮች ልብሶቻቸውን ቀድደው ተመልሰው፥ “የአቤሴሎም አሽከሮች እርሻህን በእሳት አቃጠሉት” ብለው ነገሩት። ኢዮአብም ተነሥቶ ወደ አቤሴሎም ወደ ቤቱ መጣና፥ “ብላቴኖችህ እርሻዬን ስለምን አቃጠሉት?” አለው። አቤሴሎምም ኢዮአብን፥ “ከጌድሶር ለምን መጣሁ? በዚያም ተቀምጬ ቢሆን ይሻለኝ ነበር ብለህ እንድትነግረው ወደ ንጉሥ እልክህ ዘንድ ወደ እኔ ና ብዬ ወደ አንተ ላክሁ፤ አሁንም የንጉሡን ፊት አላየሁም፤ ኀጢአት ቢኖርብኝ ይግደለኝ” አለው። ኢዮአብም ወደ ንጉሥ መጥቶ ነገረው፤ አቤሴሎምንም ጠራው፥ ወደ ንጉሡም ገብቶ ሰገደለት፤ በንጉሡም ፊት ወደ ምድር በግንባሩ ወደቀ፤ ንጉሡም አቤሴሎምን ሳመው።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 14:1-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች