እግዚአብሔርም ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፤ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፥ “በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ፥ አንዱም ድሃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ የበግና የላም መንጋ ነበረው። ለድሃው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፤ ተንከባከባትም፤ ከእርሱና ከልጆቹ ጋር አደገች፤ ከእንጀራውም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበረ፤ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሃውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ ተቈጣ፤ ዳዊትም ናታንን፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው ሞት የሚገባው ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት አድርጎ ይመልስ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “ይህን ያደረገ ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፤ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጤያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፤ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጤያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘለዓለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ከቤትህ ክፉ ነገርን አስነሣብሃለሁ፤ ሚስቶችህንም በዐይኖችህ እያየህ እወስዳለሁ፤ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፤ በዚችም ፀሐይ ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፤ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።” ዳዊትም ናታንን፥ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “እግዚአብሔር ደግሞ ኀጢአትህን አርቆልሃል፤ አትሞትምም። ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች መነሣሣት ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል” አለው። ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ። እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈው፤ እጅግም ታምሞ ነበር። ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአሔርን ለመነ፤ ዳዊትም ጾመ፤ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፤ እርሱ ግን እንቢ አለ፤ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ብላቴኖች፥ “ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፤ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በራሱ ላይ ክፉ ያደርጋል” ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። ዳዊትም ብላቴኖቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ ዐወቀ፤ ዳዊትም ብላቴኖቹን፥ “ሕፃኑ ሞቶአል?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሞቶአል” አሉት። ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፤ ተቀባም፤ ልብሱንም ለወጠ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራም አምጡልኝ አለ፤ በፊቱም እንጀራ አቀረቡለት፤ በላም። ብላቴኖቹም፥ “ይህ ስለ ሕፃኑ ያደረግኸው ነገር ምንድን ነው? እርሱ በሕይወት ሳለ ጾምህና አለቀስህ፤ እንቅልፍም አጣህ፤ ሕፃኑ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ፤ ጠጣህም” አሉት። ዳዊትም፥ “ሕፃኑ ሕያው ሳለ፤ ምናልባት እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ፤ አለቀስሁም። አሁን ግን ሞቶአል፤ የምጾመው ስለ ምንድን ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም” አለ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 12:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች