መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ካልእ 6:8-17

መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ካልእ 6:8-17 አማ2000

የሶ​ር​ያም ንጉሥ ከእ​ስ​ራ​ኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ቹም ጋር ተማ​ክሮ፥ “በዚህ ስውር ቦታ ተደ​ብ​ቀን እና​ድ​ራ​ለን።” አላ​ቸው። ኤል​ሳ​ዕም፥ “ሶር​ያ​ው​ያን በዚያ ተደ​ብ​ቀ​ዋ​ልና በዚያ ስፍራ እን​ዳ​ታ​ልፍ ተጠ​ን​ቀቅ” ብሎ ወደ እስ​ራ​ኤል ንጉሥ ላከ። የእ​ስ​ራ​ኤ​ልም ንጉሥ ኤል​ሳዕ ወደ ነገ​ረው ስፍራ ላከ፤ አንድ ጊዜም ሳይ​ሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይ​ሆን በዚያ ራሱን አዳነ። የሶ​ር​ያም ንጉሥ መን​ፈስ ስለ​ዚህ እጅግ ተበ​ሳ​ጨች፤ አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹ​ንም ጠርቶ፥ “ለእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ ማን እን​ደ​ሚ​ነ​ግ​ረው አት​ነ​ግ​ሩ​ኝ​ምን?” አላ​ቸው። ከአ​ገ​ል​ጋ​ዮ​ቹም አንዱ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በእ​ስ​ራ​ኤል ሀገር ነቢዩ ኤል​ሳዕ ያለ አይ​ደ​ለ​ምን? በእ​ል​ፍ​ኝህ ውስጥ ሆነህ የም​ት​ና​ገ​ረ​ው​ንና ቃል​ህን ሁሉ ለእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ እርሱ ይነ​ግ​ረ​ዋል፤” አለ። እር​ሱም፥ “ልኬ አስ​ይ​ዘው ዘንድ ሄዳ​ችሁ ወዴት እንደ ሆነ ዕወቁ፤” አለ። እነ​ር​ሱም፥ “እነሆ፥ በዶ​ታ​ይን አለ” ብለው ነገ​ሩት። ወደ​ዚ​ያም ፈረ​ሶ​ች​ንና ሰረ​ገ​ሎ​ችን ብዙም ጭፍራ ላከ፤ በሌ​ሊ​ትም መጥ​ተው ከተ​ማ​ዪ​ቱን ከበ​ቡ​አት። የኤ​ል​ሳ​ዕም ሎሌ ማለዳ ነቃ፤ ተነ​ሥ​ቶም በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከ​ተ​ማ​ዪቱ ዙሪያ ጭፍ​ሮች ከተ​ማ​ዋን ከብ​በ​ዋት አየ። ፈረ​ሶ​ችና ሰረ​ገ​ሎ​ችም ነበሩ። ሎሌ​ውም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እና​ድ​ርግ?” አለው። እር​ሱም፥ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእ​ነ​ርሱ ጋር ካሉት ይበ​ል​ጣ​ሉና አት​ፍራ” አለው። ኤል​ሳ​ዕም፥ “አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዐይ​ኖ​ቹን፥ እባ​ክህ፥ ግለጥ” ብሎ ጸለየ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የብ​ላ​ቴ​ና​ውን ዐይ​ኖች ገለጠ፤ እነ​ሆም፥ የእ​ሳት ፈረ​ሶ​ችና ሰረ​ገ​ሎች በኤ​ል​ሳዕ ዙሪያ ተራ​ራ​ውን ሞል​ተ​ውት አየ።