መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 5
5
ንዕማን ከለምጽ እንደ ነጻ
1የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ፥ በጌታው ዘንድ ታላቅና ክቡር ሰው ነበረ፤ ሰውዬውም ጽኑዕ፥ ኀያል ነበረ፤ ነገር ግን ለምጻም ነበረ። 2ከሶርያውያንም ጋር ወደ ሰልፍ በወጣ ጊዜ ከእስራኤል ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማረከ፤ ለሚስቱም አገልጋይ አደረጋት። 3እመቤቷንም፥ “ጌታዬ በሰማርያ ወደሚኖረው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ነቢዩ ይሄድ ዘንድ በተገባው ነበር፤ ከለምጹም በፈወሰው ነበር” አለቻት። 4ሚስቱም ወደ እርሱ ገብታ፥ “ከእስራኤል ሀገር የመጣች ይች ብላቴና እንደዚህና እንደዚህ አለች” ብላ ነገረችው።#ዕብ. “ንዕማንም ገብቶ ለጌታው ከእስራኤል ሀገር የሆነች አንዲት ብላቴና እንዲህና እንዲህ አለች ብሎ ነገረው” ይላል። 5የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን፥ “ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ” አለው። እርሱም ሄደ፤ ዐሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወቄት ወርቅ፥ ዐሥርም መለወጫ ልብስ በእጁ ወሰደ። 6ወደ እስራኤልም ንጉሥ፦ ደብዳቤውን አደረሰ። ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፥ “ደብዳቤው ካንተ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ባለሟሌን ንዕማንን ወደ አንተ ልኬዋለሁና ከለምጹ ፈውሰው።” 7የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ፥ “ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ነኝን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያት እንደሚፈልግብኝ ተመልከቱ” አለ።
8ኤልሳዕም የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ፥ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ንዕማን ወደ እኔ ይምጣ፤ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል” ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ። 9ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፤ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ። 10ኤልሳዕም፥ “ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ተጠመቅ፤ ሰውነትህም ይፈወሳል፤ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ” ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ። 11ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር። 12የደማስቆ ወንዞች ባብናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? ሄጄስ በእነርሱ ውስጥ መጠመቅና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን?” ብሎ በቍጣ ተመልሶ ሄደ። 13አገልጋዮቹም ወደ እርሱ መጥተው፥ “ነቢዩ ታላቅ ነገር ቢነግርህ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ፦ ተጠመቅና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ!” ብለው ተናገሩት። 14ንዕማንም ወረደ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ተጠመቀ፤ ሰውነቱም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሰውነት ሆኖ ተመለሰ፤ ንጹሕም ሆነ።
15እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ ኤልሳዕ ተመለሰ፤ ወደ እርሱም ደርሶ በፊቱ ቆመና፥ “እነሆ፥ በእስራኤል ነው እንጂ በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ ዐወቅሁ፤ አሁንም ከአገልጋይህ በረከት ተቀበል” አለው። 16ኤልሳዕም፥ “በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም” አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ። 17ንዕማንም፥ “እኔ አገልጋይህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ለአገልጋይህ ይስጡት። 18እግዚአብሔርም የእኔን የአገልጋይህን ኀጢአት በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬማን ቤት በገባና በሰገደ ጊዜ፥ እኔም በሬማን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር እኔን አገልጋይህን ይቅር ይለኛል” አለ። 19ኤልሳዕም ንዕማንን፥ “በሰላም ሂድ” አለው። ጥቂት መንገድም ከእርሱ ራቀ።
ግያዝ ከንዕማን ገንዘብና ልብስ እንደ ተቀበለና በኤልሳዕ እንደ ተረገመ
20የኤልሳዕም ሎሌ ግያዝ፥ “ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፤ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተኋላው እሮጣለሁ፤ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ” አለ። 21ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ዘወር ብሎ ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ፥ “ሁሉ ደኅና ነውን?” አለው። 22እርሱም፥ “ሁሉ ደኅና ነው፦ አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑ ሁለት ጐልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም ሀገር ወደ እኔ መጥተዋልና፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ” አለው። 23ንዕማንም፥ “ሁለት የብር መክሊት ውሰድ” አለው፤ ሁለቱንም መክሊት ብር ተቀብሎ በሁለት ከረጢት ውስጥ ጨመረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ። 24ወደ ስውር ቦታም በደረሱ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ። 25ከዚህም በኋላ ገብቶ፥ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም፥ “ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ?” አለው። እርሱም፥ “እኔ አገልጋይህ ወዴትም አልሄድሁም” አለ። 26እርሱም፥ “ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? አሁንም ወርቁንና ልብሱን፥ ተቀብለሃል፤ ለወይን ቦታ፥ ለመሰማርያ ቦታና ለዘይት ቦታ፥ ለላሞችና ለበጎች፥ ለወንዶችና ለሴቶች ባሮች ይሁንህ። 27ነገር ግን የንዕማን ለምጽ በአንተና በዘርህ ላይ፥ ለዘለዓለም ይመለስ” አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 5: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ