ሕዝቅያስም በነገሠ በዐሥራ አራተኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ወደ ይሁዳ ወደ ተመሸጉት ከተሞች ሁሉ ወጣ፤ ወሰዳቸውም። የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ፥ “በድያለሁ፥ ከእኔ ተመለስ፤ የምትጭንብኝንም ሁሉ እሸከማለሁ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ለኪሶ መልእክተኞችን ላከ። የአሦርም ንጉሥ በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ላይ ሦስት መቶ መክሊት ብርና ሠላሳ መክሊት ወርቅ ጫነበት። ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብር ሁሉ ሰጠው። በዚያን ጊዜም ሕዝቅያስ ከእግዚአብሔር መቅደስ ደጆችና የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከለበጣቸው መቃኖች ወርቁን ቈረጠ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠው። የአሦርም ንጉሥ ተርታንንና ራፌስን ራፋስቂስንም ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ወደ ኢየሩሳሌም ላካቸው። ወጥተውም ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ፤ በአጣቢውም እርሻ መንገድ ባለችው በላዪኛዪቱ ኩሬ መስኖ አጠገብ ቆሙ። ሕዝቅያስንም ጠሩ፤ የቤቱም አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም ጸሓፊውም ሳምናስ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ወደ እነርሱ ወጡ። ራፋስቂስም አላቸው፥ “ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ ንጉሥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የምትተማመንበት መተማመኛ ምንድን ነው? የከንፈር ቃል ለሰልፍ ምክርና ኀይል እንደሚሆን ትናገራለህ፤ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸምበቆ በትር በግብፅ ትታመናለህ፤ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል፥ ያቈስለውማል፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። እናንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትሉኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በኢየሩሳሌም ባለው በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁንም እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፤ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ቢቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሶች በግብፅ ስትታመን፥ ከጌታዬ አገልጋዮች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትመልስ ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? አሁን በውኑ ያለ እግዚአብሔር ትእዛዝ ይህን ስፍራ እናጠፋ ዘንድ ወጥተናልን? እግዚአብሔር፦ ወደዚች ሀገር ወጥታችሁ አጥፉአት አለን።” የኬልቅዩም ልጅ ኤልያቄም ሳምናስም ዮአስም ራፋስቂስን፥ “እኛ እንሰማለንና በሱርስት ቋንቋ ለአገልጋዮችህ ተናገር፤ በዕብራይስጥም ቋንቋ አትናገረን፤ በቅጥርም ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው ቋንቋ ለምን ትናገራለህ?” አሉት። ራፋስቂስ ግን፥ “በውኑ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ እናንተና ወደ ጌታችሁ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡት ሰዎች አይደለምን?” አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፥ “የታላቁን የአሦር ንጉሥ ቃል ስሙ፤ ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፤ ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል፤ ይህችንም ከተማ የአሦር ንጉሥ ሊይዛት አይችልም እያለ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፤ የአሶር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ፤ ወደ እኔም ውጡ፤ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፤ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፤ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን፥ ወይራና ማር ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ በሕይወት እንድትኖሩ፥ እንዳትሞቱም ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድናችኋል ብሎ ያታልላችኋልና አትስሙት። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የኤማትና የአርፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፋሩዋይምና የሄና የዒዋም አማልክት ወዴት አሉ? ስማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድናት ዘንድ ከሀገሮቹ አማልክት ሁሉ ሀገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?” ሕዝቡም ዝም አሉ፥ አንዳችም ቃል አልመለሱለትም፤ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና። የቤቱ አዛዥ የኬልቅዩ ልጅ ኤልያቄም፥ ጸሓፊው ሳምናስ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሳፍ ልጅ ዮአስ ልብሳቸውን ቀድደው ወደ ሕዝቅያስ ገቡ፥ የራፋስቂስንም ቃል ነገሩት።
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 18 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 18:13-37
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች