መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 8
8
ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ መጣ
1ከዚህም በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ መጣ፤ እርሱም የሠራያ ልጅ፥ የአዛርያስ ልጅ፥ የኬልቅዩ ልጅ፥ የሴሎም ልጅ፤ 2የሳዶቅ ልጅ፥ የአኪጦብ ልጅ፥ የአማርትዩ ልጅ፥ የአዝያን ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ የአቢሱ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የአልዓዛር ልጅ፥ የመጀመሪያው ካህን የአሮን ልጅ፤ 3ይህም ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ የሰጠውን የሙሴን ኦሪት ሁሉ ያውቅ ነበረ፤ እርሱም ጸሓፊ ነበር። 4ንጉሡም ክብርን ሰጠው፤ በፊቱ ባለሟልነትን አግኝትዋልና፥ በሁሉም ላይ ሹሞታልና። 5ከእስራኤልም ልጆች፥ ከካህናቱና ከሌዋውያኑ፥ ከመዘምራኑና ከበረኞች፥ ከቤተ መቅደስ አገልጋዮችም፥ ዐያሌዎቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 6በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመተ መንግሥቱ፥ በአምስተኛው ወር፥ በወሩ መባቻ ከባቢሎን ወጡ፤ እግዚአብሔርም መንገዳቸውን እንዳቀናላቸው በመጀመሪያው ወር መባቻ ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 7ዕዝራም ብዙ ትምህርት የሚያውቅ ነበረ፤ ለእስራኤልም ሥርዐትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ከእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ የሚጐድለው አልነበረም።
ንጉሥ አርጤክስስ ለዕዝራ የሚፈልገው ሁሉ እንዲደረግለት የሰጠው ትእዛዝ
8ንጉሡ አርጤክስስም ወደ ካህኑና የእግዚአብሔርን ሕግ ወደሚጽፈው ወደ ዕዝራ ደብዳቤ ላከ። ከአርጤክስስም የእግዚአብሔርን ሕግ ወደሚጽፈው ወደ ካህኑ ዕዝራ የተላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ 9“ከንጉሠ ነገሥት ከአርጤክስስ ለእግዚአብሔር ሕግ ጸሓፊ፥ ለካህኑ ለዕዝራ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ 10እኔ ሰውን በመውደድ አስቤ ከአይሁድ ወገን በመንግሥቴ ካሉ ከካህናትና ከሌዋውያን ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ዘንድ የሚወዱትን ሁሉ ከአንተ ጋር ይሂዱ ብዬ አዝዣለሁ። 11ወደ ኢየሩሳሌምም ይሄዱ ዘንድ የሚወዱ ሁሉ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን አይተው ከእናንተ ጋር ይተባበሩ። 12እንደ እግዚአብሔር ሕግ ሄደው ያደርጉ ዘንድ እኔና ሰባቱ ባለሟሎች፥ አማካሪዎችም እንዲህ አዝዘናል። 13እኔና ባለሟሎች የተሳልነውን ቍርባን፥ በባቢሎን ሀገር የተገኘውንም ወርቁንና ብሩን ሁሉ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ፥ 14ሕዝቡ በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከሚያገቡት ስእለት ጋራ ወርቁንና ብሩን፥ ለበሬዎች፥ ለፍየሎችና ለበጎች መግዣ ይሰብስቡ፥ 15እንደ ሥርዐታቸው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር መሠዊያ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ፥ 16ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ፥ ከባልንጀራህ ጋር ታደርገው ዘንድ የምትወደውን ሁሉ በዚህ ወርቅና ብር እንደ አምላክህ ፈቃድ አድርግ። 17በኢየሩሳሌም ላለ ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ግዳጅ የሚሆነውን ንዋያተ ቅድሳት። 18ለአምላክህ ቤተ መቅደስ ግዳጅ የምትሻው ሌላም ቢኖር ከንጉሡ ዕቃ ቤት እሰጣለሁ።
19“እኔ ንጉሥ አርጤክስስ የልዑል እግዚአብሔርን ሕግ የሚጽፍ ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቀውን ሁሉ በሶርያና በፊንቂስ ካለው ዕቃ ቤት እንዲሰጡት አዘዝሁ። ስጡ፤ እንቢም አትበሉ። 20እስከ መቶ መክሊት ብር፥ ዳግመኛም እስከ መቶ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶም የኔባል መስፈሪያ ወይን፥ ብዙ ጨውም ቢሆን ስጡ። 21በንጉሥ መንግሥትና በልጆቹ ላይ መከራ እንዳይመጣ በልዑል እግዚአብሔር ሕግ ይሥሩ። 22ከካህናቱና ከሌዋውያኑ፥ ከመዘምራኑና ከበረኞቹ ግብር አትቀበሉ። ከቤተ መቅደስም አገልጋዮች፥ ተቀጥረው ቤተ መቅደስን ከሚያገለግሉ ሁሉ ምንም አትቀበሉ፥ አትግዟቸውም።
23“አንተም ዕዝራ! እግዚአብሔር በገለጠልህ ጥበብ የአምላክን ሕግ ከሚያውቁ ወገኖች ውስጥ ሶርያንና ፊንቂስን የሚገዙ መኳንንቱንና መሳፍንቱን ሹም፤ የእግዚአብሔርን ሕግ የማያውቁትንም አስተምራቸው። 24የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ትእዛዝ የሚተላለፈውንም ሁሉ ቸል አትበሉ፤ ቅጡ፤ በሞትም ቢሆን፥ በግርፋትም ቢሆን፥ በባርነትም ቢሆን፥ በመውረስም ቢሆን፥ ሁሉንም በየኀጢአቱ ቅጡት።”
ዕዝራ አምላኩን እንዳመሰገነ
25ዕዝራም እንዲህ አለ፥ “በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ያከብር ዘንድ ይህን ነገር በንጉሥ ልብ ያሳደረ እግዚአብሔር ይመስገን። 26በነገሥታቱና በአማካሪዎቹ፥ በወዳጆቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እኔን አክብሮኛልና። 27ከዚህም በኋላ በፈጣሪዬ በእግዚአብሔር ጸጋ ታመንሁ። ከእኔም ጋር ይወጡ ዘንድ ከእስራኤል ሰዎችን ወሰድሁ።”
ከምርኮ የተመለሱ
28በንጉሡ በአርጤክስስ መንግሥት በየሀገራቸውና በየአውራጃቸው ግዛት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የወጡ አለቆችም እነዚህ ናቸው። 29ከፎሮስ ልጆች ጣስጣሞስ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከፊንሐስ ልጆች ጌርሳም” ይላል። ከኢዮጥማሩም ልጆች ጋሜሎስ፥ ከዳዊትም ልጆች የሴኬንያስ ልጅ አጡስ፥ 30ከፋሬስም ልጆች ዘካርያስ፥ ከእርሱም ጋር መቶ አምሳ ሰዎች ተቈጠሩ። 31ከፎአት ሞዓብም ልጆች የዛርያ ልጅ ኤሊዎንያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰዎች። 32ከዘቶይስም ልጆች የኢያሐቲሉ ልጅ ኢያኬንያስ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ሰዎች፥ ከአዲኑ ልጆች የዮናታን ልጅ ኦቤድ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ አምሳ ሰዎች። 33ከኤላም ልጆች የጎቶልያ ልጅ ኢሴይ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ሰዎች። 34ከሳፋጢ ልጆች የሚካኤል ልጅ ዛርያስ፥ ከእርሱም ጋር ሰባ ሰዎች። 35ከኢዮአብም ልጆች የኢዝኤል ልጅ ኦባድያ፥ ከእርሱም ጋር ሁለት መቶ ዐሥራ ሁለት ሰዎች። 36ከባኒ ልጆችም የኢዮሳፌይ ልጅ አስሊሞት፥ ከእርሱም ጋር መቶ ስድሳ ሰዎች። 37ከቤዔር ልጆችም የባቢ ልጅ ዘካርያስ፥ ከርሱም ጋር ሃያ ስምንት ሰዎች። 38ከአሰጣያትም ልጆች የአዝጋድ ልጅ ዮሐንስ፥ ከርሱም ጋር መቶ ዐሥር#“መቶ ኀምሳ” የሚል የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። ሰዎች። 39ከአዶኒቃም ልጆች የቀሩት ሁሉ ስማቸው ይህ ነው፦ ኤሊፋሊ፥ ይዑኤል፥ ሰሚያስ፥ ከእነርሱም ጋራ ሰባ#“መቶ” የሚል የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። ሰዎች። 40ከቤኑስም ልጆች የአስጣስቆሩ ልጅ ዑታይ ከእርሱም ጋራ ሰባ ሰዎች ተቈጠሩ።
ዕዝራ የቤተ መቅደስ ካህናትና ሌዋውያንን እንዳገኘ
41ቴራን ወደሚባል ወንዝም ሰበሰብኋቸው፤ በዚያም ሦስት ቀን አደርን፤ አስቈጠርኋቸውም። 42ከውስጣቸውም ካህናትንና ሌዋውያንን አላገኘንም። 43ወደ አልዓዛርም ላክሁ፤ ከእኔም ጋር መአስመንን፥ አንዐጣንን፥ ሰምያስን፥ ኢዮሪቦን፥ ናታንን፥ አርጦንን፥ ዘካርያስን፥ ሞሱላሞስን ወሰድሁ። 44ከእነርሱም ጋር ከመሳፍንቶቻቸውና ከዐዋቂዎቻቸው ወሰድሁ። 45ወደ ዕቃ ቤቱም ሹም ወደ ያድዮን ይሄዱ ዘንድ ነገርኋቸው። 46ለእግዚአብሔርም ቤት ካህናትን እንዲልኩልን ለያድዮንና ለወንድሞቹ፥ በዚያም ቦታ ለአሉ ሰዎች ይነግሯቸው ዘንድ አዘዝኋቸው። 47ከእስራኤል ልጅ ከሌዊ ልጅ ከሞሐሊ ልጆች ጠቢባን ሰዎችን አሲብያንና ልጆቹን፥ ዐሥራ ስምንት ወንድሞቹንም አመጡልን፥ 48ከከዓኑ ልጆችና ከልጆቻቸውም ውስጥ የሆኑ ሃያ ሰዎች፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከካናኔዎስ ልጆች አሴቢያ አኑዮስ አሲያስ” ይላል። 49ዳዊት የሠራቸው የቤተ መቅደስ አገልጋዮችና አለቆቻቸው ለሌዋውያን ሥራ የተጨመሩ የካህናት ልጆች ሁለት መቶ ሃያ ናቸው፤ የሁሉም ስማቸው ተጻፈ።
ዕዝራ ጾምን እንዳወጀ
50በአምላካችን በእግዚአብሔርም ፊት ከልጆቻችን ጋራ በዚያ እንጾም ዘንድ ለልጆቻችንና ለከብቶቻችንም ይቅርታን እንለምን ዘንድ ተሳልን። 51ሀገራችንን የሚያጸኑና ከጠላቶቻችን ጋራ የሚመካከቱ እግረኞችንና ፈረሰኞችን እንዲሰጠን ለንጉሡ እልክ ዘንድ አፍሬአለሁና። 52ሥራውን ሁሉ ያቀናላቸው ዘንድ ከሚፈልጉት ሰዎች ጋራ የጌታችን ከሃሊነት እንደሚኖር ለንጉሡ ነግረነው ነበርና። 53ዳግመኛም ስለዚህ ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ለመን፤ እርሱም ይቅር አለን።
ለቤተ መቅደስ ሥራ የቀረበ መባእ
54ከሕዝቡና ከካህናቱ ሹሞች ዐሥራ ሁለቱን ሰዎች፥ ኤሴርያንና አሴሚያን፥ ከእነርሱም ጋር ከወንድሞቻቸው መካከል ዐሥር ሰዎችን ለየሁ። 55ንጉሡና መኳንንቱ፥ አማካሪዎቹም እስራኤልም ሁሉ የሰጡንን ወርቁንና ብሩን የእግዚአብሔርንም ቤት ንዋየ ቅድሳት መዝኜ ሰጠኋቸው። 56ስድስት መቶ አምሳ መክሊት ብርም መዝኜ ሰጠኋቸው። 57መቶ መክሊት የብር ዕቃ፥ መቶ መክሊትም ወርቅ፥ ሃያ መክሊትም የወርቅ ዕቃ፥ የሚወደድ እንደ ወርቅም የጠራና የጠነከረ ዐሥራ ሁለት የናስ ዕቃ መዝኜ ሰጠኋቸው። 58እንዲህም አልኋቸው፥ “እናንተም ለእግዚአብሔር ተለዩ፥ ለአባቶቻችን ፈጣሪ ለእግዚአብሔር ስእለት የሆነውን የብሩንና የወርቁን ንዋየ ቅድሳትም ለዩ። 59ለመሳፍንቱና ለመኳንንቱ፥ ለካህናቱ አለቆችና ለሌዋውያኑ፥ ለእስራኤልም ሀገሮች አለቆች በኢየሩሳሌም በአምላካችን ቤት አዳራሽ ውስጥ እስክትሰጧቸው ድረስ ተግታችሁ ጠብቁ።” 60ካህናቱና ሌዋውያኑም የተቀበሉትን ወርቁንና ብሩን፥ የኢየሩሳሌምንም ንዋየ ቅድሳት ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገቡ።
ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ሕዝብ
61በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቴራን ከሚባል ሀገር ተነሡ፤ ከጠላቶቻችን ሁሉ ባዳነን፥ በፈጣሪያችን ከእኛ ጋር ባለች ጽንዕት እጅም ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። 62በደረሱ በሦስተኛውም ቀን ወርቁንና ብሩን መዝነውና ቈጥረው በቤተ እግዚአብሔር ለኦርያ ልጅ ለካህኑ ለመርሞቲዮራ ሰጡት። 63የሁሉም ልኩ፥ ሚዛኑም ያንጊዜ ተጻፈ። 64ከእርሱም ጋር የፊንሐስ ልጅ አልዓዛር ነበረ፤ ከእነርሱም ጋር ሌዋውያኑ የኢያሱ ልጅ የዘባትና የብኑ ልጅ ሞኢተስ ነበሩ። 65ከምርኮ የተመለሱትም ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረቡ። ዐሥራ ሁለት ኮርማዎችን፥ ዘጠና ስድስት በጎችን፥ 66ስለ ድኅነትም ሰባ ስድስት ሙክቶችን፥ ዐሥራ ሁለት የበግ ጠቦቶችን፥ ሁሉንም ለእግዚአብሔር ሰዉ። 67ከዚህም በኋላ ለንጉሡ ዕቃ ቤት ሹሞች፥ ለሶርያና ለፊንቂ ገዦችም ከንጉሡ የመጣውን ደብዳቤ ሰጧቸው፤ ሕዝቡንና የእግዚአብሔርንም መቅደስ አከበሩ።
ዕዝራ ከአሕዛብ ጋር የተደረገውን ጋብቻ እንደ ተቃወመ
68ከዚህም በኋላ ሹሞች መጥተው የሠሩትን ነገሩኝ። 69እንዲህም አሉኝ፥ “የእስራኤል ወገኖች፥ መኳንንቶቻቸውም፥ ካህኖቻቸውም፥ ሌዋውያኑም ከሌሎች የምድር አሕዛብ ከከናኔዎን፥ ከፌሬዜዎን፥ ከኬጤዎንም፥ ከኢያቡሴዎን፥ ከሞዓባውያን፥ ከግብፃውያንና ከኤዶሜዎን ርኵሰት አልተለዩም። 70ሴቶች ልጆቻቸውን አገቡ፤ እነርሱና ልጆቻቸውም የከበረውን ዘር ከባዕዳን የምድር አሕዛብ ጋር ቀላቀሉ፤ መሳፍንቶቻቸውና መኳንንቶቻቸውም ከመጀመሪያው ሥራቸው ጀምሮ በዚያች ኀጢአት አንድ ሆኑ።” 71ከዚህም በኋላ ይህን በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና ልብሰ ተክህኖዬን ቀደድሁ፤ የራሴን ጠጕርና ጢሜንም ነጨሁ፤ ተክዤና አዝኜም ተቀመጥሁ። 72እኔም በዚያች ኀጢአት አዝኜና ተክዤ ተቀምጬ ሳለሁ የእስራኤል ፈጣሪ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ። 73ከዚህም በኋላ በሠርኩ መሥዋዕት ጊዜ ጾመኛ እንደ ሆንሁ ልብሴና የክህነት ልብሴ እንደ ተቀደደ ሆኖ ተነሣሁ፤ በጉልበቴም ተንበረከክሁ፤ እጆችንም ወደ እግዚአብሔር ዘረጋሁ። 74እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ ከፊትህ የተነሣ አፍራለሁ፤ እፈራለሁም። 75ኀጢአታችን በዝትዋልና፥ ከራሳችንም ከፍ ከፍ ብሏልና፥ አለማወቃችንም እስከ ሰማይ ደርሷልና። 76ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቅ ኀጢአት ላይ ኖረናል። 77በእኛ ኀጢአትና በአባቶቻችንም ኀጢአት የምድር ነገሥታት ከወንድሞቻችንና ከንጉሦቻችን፥ ከካህኖቻችንም ጋር ማረኩን፤ በጦራቸውም ዘረፉን፤ እስከ ዛሬም ድረስ አፈርን። 78አሁን ግን በዚያች በተቀደሰችው ቦታህ ሥርንና ስምን ትተውልን ዘንድ እግዚአብሔር ሆይ ቸርነትህ በእኛ ላይ በዝታ ተደረገችልን። 79በአንተም በአምላካችን ቤት ብርሃን ተገለጠልን፤ ተገዥዎችም በሆንን ጊዜ ምግባችንን ሰጠኸን። 80በተገዛንም ጊዜ አንተ አምላካችን አልተውኸንም፤ በፋርስ ነገሥታትም ፊት ሞገስን ሰጠኸን፤ ምግባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ 81ቤተ መቅደሳችንንም ያከብሩ ዘንድ፥ የጽዮንንም ፍራሿን ይሠሩ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ኀይልን ይሰጡን ዘንድ አልተውኸንም።
82“አቤቱ፥ አሁንስ ይህ በእኛ ላይ ሳለ ምን እንላለን? በባሮችህ በነቢያትም እጅ እንዲህ ስትል የሰጠኸውን ትእዛዝህን ካድን። 83ትወርሷት ዘንድ ወደ እርሷ ትገባላችሁ ያልሃቸው ያች ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት የተዳደፈች ምድር ናት፤ ርኵሰታቸውንም መሏት። 84ሴቶች ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አታጋቡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አታጋቡ፤ 85ድል ትነሷቸው ዘንድ፥ የምድርንም በረከት ትበሉ ዘንድ፥ ለልጆቻችሁ ለዘለዓለሙ ታወርሷት ዘንድ በዘመናችሁ ሁሉ ከእነርሱ ጋር አትስማሙ። 86ይህችም ያገኘችን ሁሉ ስለ ሥራችን ክፋትና ስለ ኀጢአታችን ብዛት ነው። 87አቤቱ አንተ ግን ኀጢአታችንን ታገሥህ፤ እንመለስም ዘንድ ሥርን ሰጠኸን፤ ዳግመኛም ሕግህን አፍርሰን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ጋር አንድ እንሆን ዘንድ ይገባናልን? 88ብትቈጣንስ ሥርንና ዘርን፥ ስማችንንም እስከማታስቀር ድረስ ባጠፋኸን ነበር። 89አቤቱ የእስራኤል አምላክ አንተ፥ እውነተኛ ነህ፥ ዛሬ ሥርን ትተህልናልና። 90አሁንም በፊትህ በኀጢአታችን አለን። ስለዚህ በፊትህ እንቆም ዘንድ አይገባንም።”
91ዕዝራም በቤተ መቅደሱ አንጻር ተንበርክኮ እያለቀሰ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያሉ ብዙ ሰዎች ሴቶችና ወንዶች፥ ቆነጃጅቱም ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፤ በሁሉም ላይ ታላቅ ልቅሶ ሆነ። 92ከእስራኤልም ልጆች ውስጥ የኢያኤል ልጅ ኢኮንያስ ዕዝራን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ “ልዩ ከሚሆኑ ከምድር አሕዛብ ወገን ሚስት ያገባን እኛ እግዚአብሔርን በድለናል፤ አሁንም ይህ ሁሉ በእስራኤል ዘንድ አለ። 93ነገር ግን እንደ ፍርድህ ልዩ ከሚሆኑ ከምድር አሕዛብ ወገን ያገባናቸውን ሚስቶቻችንን ሁሉ ከልጆቻቸው ጋራ ከእኛ እናስወጣቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ስም እንማማል። 94የእግዚአብሔርን ሕግ የሚወዱ ሰዎችንም ሁሉ ተነሥተህ አምላቸው። 95ይህ ሥራ ባንተ ላይ ነውና፥ እኛም ካንተ ጋር ነንና፥ እንረዳሃለንምና።” 96ዕዝራም ተነሥቶ የሕዝቡን ሹሞችና ካህናቱን፥ ሌዋውያኑንም፥ እስራኤልንም ሁሉ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አማላቸው፤ እነርሱም ማሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ