መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 1
1
ሰሎሞን ጥበብን ከእግዚአብሔር እንደ ለመነ
(1ነገ. 3፥1-15)
1የዳዊት ልጅ ሰሎሞንም በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፤ እጅግም አከበረው፤ አገነነውም። 2ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ሁሉ ተናገረ። 3ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር የምስክር ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታው መስገጃ ሄዱ። 4ዳዊት ግን የእግዚአብሔርን ታቦት ከቂርያትይዓሪም አወጣት። ለእርሷ በኢየሩሳሌም ድንኳን አዘጋጅቶላት ነበርና። 5የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንና የእስራኤልም ጉባኤ የእግዚአብሔርን ታቦት ይፈልጓት ነበር።#አንዳንድ የግሪክ ሰባ. ሊ. ዘርዕ “እግዚአብሔርን በዚያ ይፈልጉት ነበር” ይላል። 6ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በድንኳኑ አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፤ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።
7በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔር ለሰሎሞን ታየው፥ “የምሰጥህን ከእኔ ለምን” አለው። 8ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው፥ “ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረትን አድርገሃል፤ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል። 9አሁንም አቤቱ አምላኬ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር#በግእዝ “ከመኆፃ ባሕር” ይላል። አሸዋ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ስምህ የታመነ ይሁን። 10አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና ማስተዋልን ስጠኝ፤ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ መፍረድ የሚቻለው የለምና።” 11እግዚአብሔርም ሰሎሞንን አለው፥ “ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትን፥ ሀብትን፥ ክብርን፥ የጠላቶችህንም ነፍስ፥ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህም፤ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ትፈርድ ዘንድ ጥብብንና ማስተዋልን ለራስህ ለምነሃል። 12ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥሃለሁ። ካንተ በፊት ለነበሩ ነገሥታት ያልተሰጠውን፥ ከአንተም በኋላ ለሚነሡ የማይሰጠውን ብልፅግናን፥ ገንዘብንና ክብርን እሰጥሃለሁ።” 13ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ኮረብታ ከምስክሩ ድንኳን ፊት ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።
የሰሎሞን ብልጽግና
(1ነገ. 10፥26-29)
14ሰሎሞንም ሰረገሎችንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፤ አንድ ሺህ አራት መቶ ሰረገሎች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችም አስቀመጣቸው። ሕዝቡም ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም ነበሩ። 15ንጉሡም ብሩንና ወርቁን፥ በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ፥ የዝግባንም እንጨት በብዛት በቆላ እንደሚገኝ ሾላ በይሁዳ አኖረ። 16የሰሎሞን ፈረሶች መምጫ ከግብፅና ከቴቁሄ ምድር ነበር። በዋጋ ገዝተው ከቴቁሄ የሚያመጡአቸውም ከሀገር ሽማግሌዎች#“ከሀገር ሽማግሌዎች” የሚለው በግሪኩ የለም። የሆኑ የሰሎሞን ነጋዴዎች ነበሩ። 17ሄደውም ከግብፅ አንድ ሰረገላ በስድስት መቶ ብር፥ አንድንም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር አመጡ፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሦርያ ነገሥታት ሁሉ በየተራቸው ያመጡላቸው ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 1: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ