የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ ሰሎሞን በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ወደ ሰማይ ዘረጋ። እንዲህም አለ፥ “የእስራኤል አምላክ አቤቱ! በላይ በሰማይ፥ በታችም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልቡ በፊትህ ለሚሄድ ባሪያህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፥ በአፍህ ተናግረህ፥ እንደ ዛሬ ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው። አሁንም የእስራኤል አምላክ አቤቱ፦ አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በፊቴ ይሄዱ ዘንድ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው ከአንተ አይጠፋም ብለህ ለአባቴ ለዳዊት ተስፋ የሰጠኽውን ጠብቅ። አሁንም የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል እባክህ እውነት ይሁን። “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለው ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ ለስምህ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ! አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ዛሬም ባሪያህ በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎት ስማ፤ ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፦ በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ሌሊትና ቀን የተገለጡ ይሁኑ። ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። “ሰው ባልጀራውን ቢበድል፥ ይምልም ዘንድ በላዩ መሐላ ቢጫንበት፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢናዘዝ፥ በሰማይ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህም በእስራኤል ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ጻድቁን አጽድቀው፤ እንደ ጽድቁም ክፈለው። “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላቶቻቸው ፊት ድል ቢሆኑ፥ ወደ አንተም ቢመለሱ፥ ለስምህም ቢናዘዙ፥ በዚህም ቤት ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። “አንተን ስለ በደሉ ሰማይ ቢዘጋ፥ ዝናብም ባይዘንብ፥ በዚህም ስፍራ ቢጸልዩ፥ ለስምህም ቢናዘዙ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ። “በምድር ላይም ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ ቢሆን፥ አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢመጣ፥ የሕዝብህም ጠላት ከከተሞቻቸው በአንዲቱ ከብቦ ቢያስጨንቃቸው፥ መቅሠፍትና ደዌ ሁሉ ቢሆን፥ ማናቸውም ሰው የልቡን ሕመም ዐውቆ ጸሎትና ምህላ ቢያደርግ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ሁሉ ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለውና ስጠው። ለአባቶቻችን በሰጠሃት ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ። “ከሕዝብህም ከእስራኤል ወገን ያልሆነ እንግዳ ስለ ስምህ ከሩቅ ሀገር ቢመጣ፥ ታላቁን ስምህን፥ ብርቱይቱንም እጅህን፥ የተዘረጋችውንም ክንድህን ሰምተው ቢመጡና በዚህ ቤት ቢጸልዩ፥ አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዝብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፥ እንደ ሕዝብህ እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። “ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትመልሳቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ከተማ፥ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት በእግዚአብሔር ስም ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው። “የማይበድልም ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላቶቻቸው አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅ ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ወደ ጠላቶች ሀገር ቢማረኩም፥ በተማረኩበትም ሀገር ሆነው በልባቸው ንስሓ ቢገቡ፥ በተማረኩበትም ሀገር ሳሉ ተመልሰው፦ ኀጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉንም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፥ በማረኩአቸው በጠላቶቻቸው ሀገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን ፥ በአንተም ላይ ያደረጉትን በደላቸውን ሁሉ ይቅር በል፤ ይራሩላቸውም ዘንድ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ስጣቸው፤ ከግብጽ ምድር ከብረት እቶን ውስጥ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸውና። በጠሩህ ጊዜ ሁሉ ትሰማቸው ዘንድ ለባሪያህና ለሕዝብህ ለእስራኤል ልመና ዐይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮዎችህ የተከፈቱ ይሁኑ። ጌታዬ እግዚአብሔር ሆይ! አባቶቻችንን ከግብፅ ባወጣህ ጊዜ በባሪያህ በሙሴ እጅ እንደ ተናገርህ ርስት ይሆኑህ ዘንድ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ለይተሃቸዋልና።” ያንጊዜም ሰሎሞን ሥራውን በጨረሰ ጊዜ ስለዚያ ቤት እንዲህ ሲል ተናገረ። “እግዚአብሔር በሰማይ ፀሐይን አሳየ፤ እግዚአብሔር በጨለማ ውስጥ እንደሚኖር ተናገረ፤ ቤቴን ሥራ፤ በመታደስም ለመኖር ለራስህ ጥሩ ቤትን ሥራ፤” ይህችስ በመሐልይ መጽሐፍ የተጻፈች አይደለምን?
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 8 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 8:22-53
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች