ኤልያስም ፈርቶ ተነሣ፤ ነፍሱንም ሊያድን ሄደ፤ በይሁዳም ወዳለው ወደ ቤርሳቤህ መጥቶ ብላቴናውን በዚያ ተወ። እርሱም አንድ ቀን የሚያህል መንገድ በምድረ በዳ ሄደ፤ መጥቶም ከደድሆ ዛፍ በታች ተቀመጠና፦ ይበቃኛል፤ አሁንም አቤቱ! እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ” ብሎ እንዲሞት ለመነ። በደድሆውም ዛፍ በታች ተኛ፤ እንቅልፍም አንቀላፋ፤ እነሆም፥ መልአክ ዳሰሰውና፥ “ተነሥተህ ብላ” አለው። ከዚህ በኋላ ኤልያስ ተነሥቶ፥ እነሆ፥ በራሱ አጠገብ የተጋገረ እንጎቻና በማሰሮ ውኃ አገኘ። በላም፤ ጠጣም፤ ተመልሶም ተኛ። የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ሁለተኛ ጊዜ መጥቶ ዳሰሰውና፥ “የምትሄድበት መንገድ ሩቅ ነውና ተነሥተህ ብላ” አለው። ተነሥቶም በላ፤ ጠጣም፤ በዚያም በበላው የምግብ ኀይል እስከ ኮሬብ ድረስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ሄደ። እዚያም ወዳለ ዋሻ ገባ፤ በዚያም አደረ፤ እነሆም፥ “ኤልያስ ሆይ! ምን አመጣህ?” የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ እርሱ መጣ። ኤልያስም፥ “ሁሉን ለሚገዛ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፤ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና፥ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋልና፥ ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና፤ እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ ነፍሴንም ሊወስዱአት ይሻሉ” አለ። እርሱም አለ፥ “ነገ ውጣ፤ በተራራውም ላይ በእግዚአብሔር ፊት ቁም። እነሆም፥ እግዚአብሔር በዚያ አለፈ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮቹን ሰነጠቀ፤ ዓለቶቹንም ሰባበረ፤ እግዚአብሔር ግን በነፋሱ ውስጥ አልነበረም። ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ ውስጥ አልነበረም። ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔርም በእሳቱ ውስጥ አልነበረም። ከእሳቱም በኋላ እንደ ፉጨት ያለ ቀጭን ድምፅ ሆነ፤ በዚያም እግዚአብሔር ነበረ።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 19:3-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች