መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ቀዳ​ማዊ 17:18-24

መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ቀዳ​ማዊ 17:18-24 አማ2000

እር​ስ​ዋም ኤል​ያ​ስን፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው ሆይ፥ እኔ ከአ​ንተ ጋር ምን አለኝ? አን​ተስ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ኀጢ​አ​ቴ​ንስ ታሳ​ስብ ዘንድ፥ ልጄ​ንስ ትገ​ድል ዘንድ ወደ እኔ መጥ​ተ​ሃ​ልን?” አለ​ችው። ኤል​ያ​ስም፥ “ልጅ​ሽን ስጪኝ” አላት፥ ከብ​ብ​ቷም ወስዶ ተቀ​ም​ጦ​በት ወደ ነበ​ረው ሰገ​ነት አወ​ጣው፤ በአ​ል​ጋ​ውም ላይ አስ​ተ​ኛው። ኤል​ያ​ስም፥ “እኔ በቤቷ ያደ​ርሁ የዚች መበ​ለት ምስ​ክ​ርዋ ጌታዬ ሆይ፥ ልጅ​ዋን በመ​ግ​ደ​ልህ ክፉ አድ​ር​ገ​ህ​ባ​ታ​ልና ወዮ​ልኝ!” ብሎ ጮኸ። በብ​ላ​ቴ​ና​ውም ላይ ሦስት ጊዜ እፍ አለ​በት፤ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “አቤቱ አም​ላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላ​ቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመ​ለስ ዘንድ እለ​ም​ን​ሃ​ለሁ” ብሎ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ጠራው። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም የኤ​ል​ያ​ስን ቃል ሰማ፤ የሕ​ፃ​ኑም ነፍስ ተመ​ለ​ሰች፥ ዳነም፤ ኤል​ያ​ስም ብላ​ቴ​ና​ውን ይዞ ከሰ​ገ​ነቱ ወደ ቤት አወ​ረ​ደው፥ ለእ​ና​ቱም ሰጣት፥ “እነሆ፥ ተመ​ል​ከች ልጅሽ ድኖ​አል” አለ። ሴቲ​ቱም ኤል​ያ​ስን፥ “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቃል በአ​ፍህ እው​ነት እንደ ሆነ አሁን ዐወ​ቅሁ” አለ​ችው።