በየዓመቱ ለሰሎሞን የሚመጣለት የወርቅ ሚዛን ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት መክሊት ወርቅ ነበረ። ይኽንም፥ ግብር የሚያስገብሩ ሰዎች፥ ነጋዴዎችም፥ በዙሪያው ያሉ ነገሥታትም ሁሉ፥ የምድርም ሹሞች ከሚያወጡት ሌላ ነው። ንጉሡ ሰሎሞንም ከጥፍጥፍ ወርቅ ሁለት መቶ አላባሽ አግሬ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም አላባሽ አግሬ ጋሻ ውስጥ የገባው ወርቅ ሦስት መቶ ሰቅል ነበረ። ከጥፍጥፍም ወርቅ ሦስት መቶ ጋሻ አሠራ፤ በአንዱም ጋሻ የገባው ወርቅ ሦስት ምናን ነው፤ ንጉሡም የሊባኖስ ዱር በተባለው ቤት ውስጥ አኖራቸው። ንጉሡም ደግሞ ከዝሆን ጥርስ ታላቅ ዙፋን አሠራ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። ወደ ዙፋንም የሚያስኬዱ ስድስት እርከኖች ነበሩ፤ በስተኋላውም ያለው የዙፋኑ ራስ ክብ ነበረ፤ በላም ምስል የተቀረጸ በወዲህና በወዲያም መደገፊያ ነበረው፤ በመደገፊያዎቹም አጠገብ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በስድስቱም እርከኖች ላይ በዚህና በዚያ ዐሥራ ሁለት አንበሶች ቆመው ነበር፤ በመንግሥታት ሁሉ እንዲህ ያለ ሥራ አልተሠራም። ንጉሡም ሰሎሞን ያሠራው የመጠጫ ዕቃ ሁሉ ወርቅ ነበረ፤ ኵስኵስቱም የወርቅ ነበረ፤ የሊባኖስ ዱር የተባለውን የዚያን ቤት ዕቃ ሁሉ በወርቅ አስለበጠው። የብርም ዕቃ አልነበረም፤ በሰሎሞን ዘመን የብር ዋጋ ዝቅተኛ ነበርና። ለንጉሡም ከኪራም መርከቦች ጋር በባሕር ውስጥ የተርሴስ መርከቦች ነበሩት፤ በየሦስት ዓመትም አንድ መርከብ ከተርሴስ ወርቅና ብር፥ የተቀረጸና የተደረደረ ዕንቍ ይዞ ይመጣ ነበር። ንጉሡም ሰሎሞን በብልጥግናና በጥበብ ከምድር ነገሥታት ሁሉ እጅግ በልጦ ነበር። የምድርም ነገሥት ሁሉ እግዚአብሔር በልቡ ያኖረለትን ጥበቡን ይሰሙ ዘንድ የሰሎሞንን ፊት ለማየት ይሹ ነበር። እነርሱም ሁሉ በዓመት በዓመቱ ገጸ በረከቱን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ፥ ልብስና የጦር መሣሪያ፥ ሽቱም፥ ፈረሶችና በቅሎዎች እየያዙ ይመጡ ነበር። ሰሎሞንም ለሰረገሎቹ ዐራት ሺህ እንስት ፈረሶች ነበሩት፤ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞችም ነበሩት፤ በሰረገሎችም ከተሞች ከንጉሡ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው። ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ፍልስጥኤም ምድርና እስከ ግብፅ ድንበር ድረስ በነገሥታቱ ሁሉ ላይ ንጉሥ ነበር። ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቆላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ። ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብፅና ከቴቁሄ ሀገር አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቴቁሄ ያመጡአቸው ነበር። አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ ኀምሳ ብር ከግብፅ ይወጣ ነበር። እንዲሁም ለኬጤዎናውያን ነገሥታትና ለሶርያ ነገሥታት ሁሉ በባሕሩ በኩል ያወጡላቸው ነበር።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 10:14-29
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች