መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 23
23
1ዳዊትም በሸመገለ ጊዜ፥ ዕድሜንም በጠገበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን በእርሱ ፋንታ በእስራኤል ላይ አነገሠው። 2የእስራኤልንም አለቆች ሁሉ፥ ካህናቱንም፥ ሌዋውያኑንም ሰበሰበ። 3ሌዋውያንም ከሠላሳ ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ ተቈጠሩ፤ ቍጥራቸውም በእያንዳንዱ ነፍስ ወከፍ ሲቈጠሩ ሠላሳ ስምንት ሺህ ነበረ። 4ከእነዚህም ውስጥ የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ የሚያሠሩት ሃያ አራት ሺህ ነበሩ፤ ስድስቱ ሺህም ጻፎችና ፈራጆች ነበሩ። 5አራቱ ሺህም በረኞች ነበሩ፤ አራቱ ሺህም ለምስጋና በተሠሩት በዜማ ዕቃዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።
6ዳዊትም እንደ ሌዊ ልጆች እንደ ጌድሶንና እንደ ቀዓት እንደ ሜራሪም በየሰሞናቸው መደባቸው። 7ከጌድሶናውያን ለአዳንና ሰሜኢ ነበሩ። 8የለአዳን ልጆች አለቃው አድሔኤል፥ ዜቶም፥ ዮሔል ሦስት ነበሩ። 9የሰሜኢ ልጆች ሰሎሚት፥ ሐዝኤል፥ ሐራን ሦስት ነበሩ። እነዚህ የለያአዳን አባቶች ቤቶች አለቆች ነበሩ። 10የሰሜኢ ልጆች ኤኢት፥ ዚዛ፥ ኢያአስ፥ በሪዓ ነበሩ። እነዚህ አራቱ የሰሜኢ ልጆች ነበሩ። 11አለቃው ኤኢት ነበረ፤ ሁለተኛው ዚዛ ነበረ፤ ኢያአስና በሪዓ ግን ብዙ ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህ እንደ አንድ አባት ቤት ሆነው ተቈጠሩ።
12የቀዓት ልጆች እንበረም፥#ዕብ. “አምራም” ሲል ግሪክ ሰባ. ሊ.“አምብራም” ይላል። ይስዓር፦ ኬብሮን፥ ዑዝኤል አራት ነበሩ። 13የእንበረም ልጆች አሮንና ሙሴ ነበሩ፤ አሮንም ለቅድስተ ቅዱሳን የተቀደሰ ይሆን ዘንድ ተመረጠ፤ እርሱና ልጆቹ ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ፊት ያጥኑና ያገለግሉ ነበር፤ በስሙም ለዘለዓለም ይባርኩ ነበር። 14የእግዚአብሔርም ሰው ሙሴና ልጆቹ በሌዊ ነገድ ተቈጠሩ። 15የሙሴ ልጆችም ጌርሳምና አልዓዛር ነበሩ። 16የጌርሳም ልጆች አለቃ ሱባኤል ነበረ። 17የአልዓዛርም ልጆች አለቃ ረዓብያ ነበረ፤ አልዓዛርም ሌሎች ልጆች አልነበሩትም፤ የረዓብያ ልጆች እጅግ ብዙ ነበሩ። 18የይስዓር ልጆች አለቃው ሰሎሚት ነበረ። 19የኬብሮን ልጆች አለቃው ኢያኤርያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው ኢያዝሔል፥ አራተኛው ኢያቄምያስ ነበሩ። 20የዑዝኤል ልጆች አለቃው ሚካ፥ ሁለተኛው ይስያ ነበሩ።
21የሜራሪ ልጆች ሞዓሊና ሐሙሲ ነበሩ። የሞዓሊ ልጆች አልዓዛርና ቂስ ነበሩ። 22አልዓዛርም ሴቶች ልጆች ብቻ እንጂ ወንዶች ልጆች ሳይወልድ ሞተ፤ ወንድሞቻቸውም የቂስ ልጆች አገቡአቸው። 23የሐሙሲ ልጆች፤ ሞዓሊ፥ አዴር፥ ኢያሪሞት ሦስት ነበሩ።
24የእግዚአብሔርን ቤት አገልግሎት በሠሩ ከሃያ አምስት#ግሪኩ “ሃያ” ይላል። ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ላይ በነበሩ በእያንዳንዳቸው በስማቸው በተቈጠሩት ላይ የአባቶች ቤት አለቆች የሆኑት በየአባቶቻቸው ቤት የሌዊ ልጆች እነዚህ ነበሩ። 25ዳዊትም እንዲህ አለ፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ዕረፍት ሰጥቶአል፤ በኢየሩሳሌምም ለዘለዓለም ይቀመጣል። 26ሌዋውያንም ከእንግዲህ ወዲህ ማደሪያውንና የማገልገያ ዕቃውን ሁሉ አይሽከሙም።” 27በመጨረሻውም በዳዊት ትእዛዝ ከሃያ አምስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት የሌዊ ልጆች ተቈጠሩ። 28የእግዚአብሔርንም ቤት በየአደባባዩና በየመጋረጃው ውስጥ ለማገልገል፥ ቅዱሱንም ዕቃ ሁሉ ለማንጻት፥ የእግዚአብሔርንም ቤት አገልግሎት ለመሥራት ከአሮን ልጆች እጅ በታች ሹሞአቸው ነበር። 29ደግሞም ገጸ ኅብስት፥ ስስ ቂጣም ቢሆን፥ በምጣድም ቢጋገር፥ ቢለወስም ለእህል ቍርባን በሆነው በመልካሙ ዱቄት በመስፈሪያና በልክ ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ ሹሞአቸው ነበር። 30በየጥዋቱና በየማታው ቆመው እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር፥ 31በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየበዓላቱም እንደ ሥርዐቱ ቍጥር በእግዚአብሔር ፊት ዘወትር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ሁሉ ለማቅረብ፥ 32ለእግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት የምስክሩን ድንኳን ሥርዐት፥ የወንድሞቻቸውን የአሮንን ልጆች ሥርዐት ለመጠበቅ ሹሞአቸው ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ