መጽሐፈ ጥበብ 13

13
የአምልኮ ጣኦት ውግዘት፦ አምልኮተ ተፈጥሮ
1እግዚአብሔርን የማያውቁ ሁሉ፥ በእውነት በባሕርያቸው ከንቱ ናቸው፤
ከሚታዩት መልካም ነገሮች፥ እርሱ የሆነውን ወደ ማወቅ አልደረሱም፤
አልያም የእጁን ሥራዎች በመመልከት፥ ሠሪውን ማስተዋል አልቻሉም።
2ነገር ግን እሳት፥ ነፋስ ወይም ፈጣን አየር፥
ከዋክብት፥ ማዕበል ወይም የሰማይ ብርሃናትን
ዓለምን ያስተዳድራሉ ብለው እንደ አማልክት ያመልኳቸው ነበር።
3ውበታቸው የሚያማልለውን ሁሉ እንደ አማልክት ቆጠሯቸው፤
እነርሱን የፈጠረና የውበት ምንጭ የሆነው ጌታ
የእነዚህ ጌታ ከእነርሱ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ አድርግ።
4በኃይላቸውና በጉልበታቸውም ተማርከው ከሆነ፥
እነርሱን የፈጠረው ደግሞ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ይግባቸው፤
5የፍጡራኑን ታላቅነትና ውበት በመመልከት፥
በንጽጽር ፈጣሪያቸው ከእነርሱ ምን ያህል የላቀ እንደሆነ ልንገምት እንችላለን።
6ምናልባት ከመንገድ የወጡት አምላክን ፍለጋ
እርሱንም ለማግኘት ካላቸው ጉጉት ሊሆን ይችላልና፥
እነኚህ ሰዎች ብዙ ሊወቀሱ አይገባም፤
7በሥራዎቹ መሀል በፍለጋ ይደክማሉ፥
ከሚታዩት ነገሮች ውበት የተነሣ
በሚያዩአቸው ነገሮች ምርኮኛ ሆነው ይቀራሉ።
8ያም ሆኖ ግን የሚያመካኙበት ነገር አይኖርም።
9ዓለምን ለመመርመር የሚበቃ ዕውቀት ካገኙ፥
ፈጣሪዋን ለማግኘት እንደምን ተሣናቸው?
አምልኮተ ጣኦት
10 # ኢሳ. 44፥9-20፤ ኤር. 10፥1-16፤ ተ.ኤር. 1፥8-73። ተስፋቸውን በሙት ነገሮች ላይ የሚያደርጉ፥
ወርቅም ይሁን ብር፥ የእንስሳት ምስሎችን፥
ጥንት በሰው እጅ የተቀረጹ ዋጋ የሌላቸው ድንጊያዎችን
የሚያመልኩ ሁሉ ምስኪኖች ናቸው።
11እንጨት ጠራቢውን ተመልከቱ፥ ለሥራው የሚስማማውን ዛፍ ይጥላል፤
ቅርፊቱን ሁሉ በጥንቃቄ ይልጣል፤ በጥበብ ጠርቦና አስተካክሎም
የቤት ውስጥ መገልገያ ያደርገዋል።
12ሲሠራ የወዳደቀውንም ቁርጥራጭ እንጨት፥
ረኃቡን የሚያስታግሥበትን ምግብ ያበስልበታል።
13ከዚህም የሚተርፍ ጐባጣና ጉጥ የበዛበት፥
ለምንም የማይሆን እንጨት ይኖራል፤
ጠራቢውም ይህን እንጨት በዕረፍት ጊዜው ይልገዋል፤
ከልምድ ባገኘው ችሎታ ያስተካክለዋል፤ በሰው ምስል ይቀርጸዋል፤
14ምናልባትም የሚያስቀይም እንስሳ መልክ ይሰጠዋል፤
በጭቃ ይለቀልቀዋል፤ ቀይ ቀለም ይቀባዋል፤
ጉድፉን ሁሉ ያጠፋለታል።
15ቀጥሎም ለእርሱ የሚስማማ ቤት ይሠራለታል፤
ወደ ግድግዳው ያሰጠጋዋል፥ በብረት ቸንክሮም ያቆመዋል።
16ራሱን መጠበቅ እንደማይችል በመረዳት፥
ምስል በመሆኑ ረዳት እንደሚያሻው ያውቅልና፤
እንዳይወድቅ በጥንቃቄ ያቆመዋል።
17ይህም ሆኖ ግን እርሱ ስለሃብቱ፥ ስለ ጋብቻው፥ ስለልጆቹ መጸለይ ቢፈልግ፥
ይህን በድን ነገር ጮኾ ሲለምን አያፍርም።
ጤናን ከደካማው፥
18ሕይወትን ከበድን፥
ችሮታን ከሰው ከማይውለው፥
ስለ ጉዞ በእግሩ እንኳ መጠቀም ከማይችል፥
19ስለ ትርፍ፥ ስለ ወደ ፊት ተግባሩና ስለሙያ ትጋቱ ጥበብን ይሰጠው ዘንድ፥
እጆቹ ከቶውንም ሰርተው ከማያውቁት ይለምናል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ