መጽ​ሐፈ ጦቢት 9

9
የሰርጉ በዓል
1ከዚህ በኋላ ጦብያ ሩፋኤልን ጠርቶ እንዲህ አለው፥ 2“ወንድሜ አዛርያ አራት አገልጋዮችና ሁለት ግመሎችን ይዘህ ወደ ራጌስ ከተማ ተጓዝ፤ 3ወደ ጋባኤልም ቤት ሂድ፥ የገንዘቡን ፊርማ አሳየውና ገንዘቡን ተቀበል፤ ጋባኤልንም ወደ ሰርጉ ግብዣ ከአንተ ጋር ይዘኸው ና፤ 4መቼም እንደምታውቀው አባቴ ቀኖቹን እየቆጠረ ነው፤ አንድ ቀን እንኳ ብዘገይ ብዙ አስጨንቀዋለሁ፤ 5ራጉኤልም እኔን ለማቆየት እንዴት እንደማለ አይተሃል፤ በመሐላው ታስሬአለሁ።” ሰለዚህ ሩፋኤል አራቱን አገልጋዮችና ሁለቱን ግመሎች ይዞ ወደ ሜዶን ወደ ራጌስ ሄደ፤ እዚያም ከጋባኤል ቤት አደሩ። ሩፋኤልም ፊርማውን ሰጠውና የጦቢት ልጅ ጦብያ እንዳገባና ወደ ሰርጉ ግብዣም እንደ ጠራው ነገረው። ጋባኤልም የገንዘብ ከረጢቶቹን በማኀተም እንደተዘጉ ቆጥሮ አስረከበውና በግመሎቹ ላይ ጫኗቸው። 6በማግስቱ ጧት በማለዳ ተነሥተው አብረው ወደ ሰርጉ ሄዱ። ወደ ራጉኤልም ቤት ሲገቡ ጦብያን በማዕድ ተቀምጦ አገኙት። ጦብያ በፍጥነት ተነሣና ጋባኤልን ሰላም አለው፤ ገባኤል እያለቀሰ እንዲህ ሲል ባረከው “አንተ ደግ ልጅ፥ የደጉ፥ የጻድቁና የለጋሱ ልጅ! ጌታ የሰማይን በረከት ለአንተና ለሚስትህ፥ ለሚስትህም አባትና እናት ይስጥ፤ የአጎቴን ልጅ የጦቢትን ሕያው አምሳል ያሳየኝ እግዝአብሔር የተባረከ ይሁን።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ