መኃልየ መኃልይ 2:1-13

መኃልየ መኃልይ 2:1-13 መቅካእኤ

እኔ የሳሮን ጽጌረዳ የቈላም አበባ ነኝ። በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በልጃገረዶች መካከል ናት። በዱር እንዳለ እንኮይ፥ እንዲሁ ውዴ በጐልማሶች መካከል ነው። ከጥላው በታች እጅግ ወድጄ ተቀመጥሁ፥ ፍሬውም ለጉሮሮዬ ጣፋጭ ነው። ወደ ወይን ጠጁም ቤት አገባኝ፥ በእኔ ላይ ያለው ዓላማውም ፍቅር ነው። በዘቢብም አጽናኑኝ፥ በእንኮይ አበረታቱኝ፥ በፍቅሩ ተነድፌ ታምሜያለሁና። ግራው ከራሴ በታች ናት፥ ቀኙም ታቅፈኛለች። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ እርሱ እስኪፈልግ ድረስ፥ ፍቅርን እንዳታስነሱትና እንዳታነሣሡት በሚዳቋ በምድረ በዳም ዋላ አስምላችኋለሁ። እነሆ፥ የውዴ ድምፅ! በተራሮች ላይ ሲዘልል በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል። ውዴ ሚዳቋን ወይም የዋላን እምቦሳ ይመስላል፥ እነሆ፥ በመስኮቶች ሲጐበኝ፥ በዓይነ ርግብም ሲመለከት፥ እርሱ ከቅጥራችን በኋላ ቆሞአል። ውዴ እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ። እነሆ፥ ክረምት አለፈ፥ ዝናቡም አልፎ ሄደ። አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የዋኔዋም ቃል በምድራችን ተሰማ። በለሱ ጐመራ፥ ወይኖችም አበቡ መዓዛቸውንም ሰጡ፥ ወዳጄ ሆይ፥ ተነሺ፥ ውቤ ሆይ፥ ነዪ።