መጽሐፈ ሲራክ 43

43
ፀሐይ
1የተራሮች መኩሪያ፥ የጠራች የሰማይ ድባብ፥ የከዋክብት ውበት፥ ሞገስ ያላትም ትዕይንት ናት። 2ፀሐይ ብቅ ስትል፥ ጮራዋንም ስትፈነጥቅ፥ የልዑል እግዚአብሔር ሥራ ምንኛ ድንቅ ነው! በማለት ታበስራለች። 3ቀትር ላይ መሬትን ታደርቃለች፤ ሙቀቷንስ የሚቋቋም ማነው? 4ሙቀትንም ለማግኘት ወናፍን መንፋት አለብን፤ ፀሐይ ግን ተራሮቹን ሦስት እጥፍ ጊዜ ታነዳቸዋለች፤ እስትንፋሷ የእሳት ነበልባል፥ ጮራዋም አንጸባራቂና ዓይንን የሚያጥበረብር ነው። 5እርሷን የፈጠረ መንገዷንም በቃሉ የሚያፈጥን፥ እግዚአብሔር ታላቅ ነው።
ጨረቃ
6ጨረቃ ቀጠሮ አክባሪ ናት፤ ጊዜያትንም ለዘለዓለም ታመለክታለች። 7በዓላትን የምታበስር፥ ከሞላች በኋላ የምትሟሟ አንጸባራቂ አካል ጨረቃ ናት። 8ወር ስሙን ከእርሷ ወረሰ፤ ወቅቷንም ጠብቃ ድንቅ መለዋወጥን ታሳያለች፤ በደመና ያሉ አእላፋት ዓርማ፤ በሰማያት ቅስትም ላይ ሆና የምታበራ ናት። ለከዋክብት 9የከዋክብት ግርማ፥ የሰማይ ውበት፥ የልዑል እግዚአብሔርም አንጸባራቂ ጌጥ ነው። 10በቅዱስ አምላክ ቃል፥ በትእዛዙ ይጸናሉ፤ በቃፊርነታቸውም ፈጽመው አይደክሙም። ቀስተ ደመና 11እጅግ ማራኪውን የቀስተ ደመናን ውበት ተመልከት፤ ፈጣሪውንም አመስግን። 12በልዑል እግዚአብሔር እጅ በሰማይ ላይ የተነደፈ አንጸባራቂ ቀስት ነው።
የተፈጥሮ ውበት
13በትእዛዙ በረዶ ይወርደል፤ መብረቁንም እንዲወነጨፍ ያደርጋል። 14ግምጃ ቤቱም ሲከፈት፥ ደመናት እንደ ወፎች ይበራሉ። 15በታላቅ ኃይሉ ደመናትን ያጠጥራል፤ ፈረካክሶም በረዶ ያደርጋቸዋል። ነጐድጓዱም በተሰማ ጊዜ ምድር ታምጣለች። 16እርሱን ባዩ ጊዜ ተራሮች ይንቀጠቀጣሉ፤ በትእዛዙም የደቡብ ነፍስ ይነፍሳል። 17የሰሜኑ ማዕበልና ዓውሎ ነፋስም እንዲሁ ናቸው። 18ለማረፍ እንደሚዘጋጅ ወፎች፥ እንዲሁ በረዶውን ያርከፈክፋል፥ እንደ አንበጣ መንጋም ያወርደዋል፤ ንጣቱ የዐይን እይታን ይማርካል፥ አወራረዱም አእምሮን ያስደምማል። 19በመሬት ላይ እንደ ጨው ሁሉ፥ የነጣ ውርጭ ያፈሳል፤ እርሱም በቀዘቀዘ ጊዜ እንደ እሾህ ይቆማል። 20ቀዝቃዛ ነፋስ ከሰሜን ይነፍሳል፤ ውሃም በረዶ ይዝላል። የረጋውንም ውሃ እንደ ጋሻ ይሸፈነዋል። 21ነፋሱ ተራሮችን ይውጣል፤ በረሃውንም ያነዳል፤ ተክሎችንም እንደ እሳት ይፈጃል። 22ደመናዎች ግን ፈጣን ፈውስን ያመጣሉ፤ ደስታን ይሰጣል። 23ጥልቁን ጉድጓድ በጥበብ ገራው፤ ደሴቶችንም ተከለበት። 24በባሕር የሚጓዙ አስፈሪነቱን ይናገራሉ፤ ትረካዎቻቸውም ጆሮዎቻችንን በአድናቆት ይሞላሉ፤ 25ያልተለመደና አስደናቂ ሥራዎች፥ ታላላቅ ፍጥረታትና እንስሳት በሙሉ በዚያም ይገኛሉና። 26እግዚአብሔር ይመስገን መልእክተኛው ከጠረፍ ይደርሳል፤ በቃሉም መሠረት ሁሉም ይፈጸማል። 27ከዚህም በበለጠ ማየት ይቻላል፤ ይሁን እንጂ በቂ አይሆንም፤ እንዲያው ባጭሩ፥ እርሱ ሁሉንም ነው። 28የእርሱን ክብር ለመግለጽ በቂ ኃይል የምናገኘው ከየት ነው? እርሱ ከሥራዎቹ ሁሉ የበለጠ ታላቅ፥ 29በጣም አስደንጋጭ እጅግ ግዙፍ፥ ኃይሉም አስደናቂ ነውና። 30በምስጋናችሁ ጌታን አወድሱት፤ የምትችሉትንም ያህል ከፍ አድርጉት፤ እርሱ ግን ከዚያም የመጠቀ ነው። በምስጋና ወቅት ኃይላችሁን ሁሉ ተጠቀሙ፤ ሰውነታችሁ አይዛል፤ ከፍጻሜው ግን ከቶውንም አትደርሱም። 31እርሱን ለመግለጽ ከቶ ያየው ይኖራልን? የሚገባውንስ ያህል ሊያከብረው የሚችለው ይኖራልን? 32ከሥራዎቹም ያየነው ጥቂቶቹን ነው፤ ከነኚህም የላቀ በርካታ ምሥጢራት አልቀረቡም። 33ሁሉን የፈጠረ ጌታ ነውና፤ ለደጋጐችም ጥበብን የሰጠ እርሱ ነውና።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ