መጽሐፈ ሲራክ 32
32
ግብዣዎች
1የክብር እንግዳ አድርገውሃልን? ብዙም አትኩራራ፥ ባሕርይህ ከሌሎች ተጋባዦች አይለይ፥ የሚፈልጉትን ሁሉ እንዳገኙ አረጋግጠህ ተቀመጥ። 2ኃላፊነትህን ከተወጣህ ወደ ቦታህ ተመለስ፤ የእነርሱ ደስታ ላንተም የደስታ ምንጭ ነው፤ ስለ መልካም ተግባርህም አክሊልን ትቀዳጃለህ። 3ሽማግሌ ሆይ! ተናገር፤ ትናገርም ዘንድ ይገባሀል፤ ንግግርህ ግን ግልጽነት ይኑረው፤ ዘፈኑንም አታበላሽ። 4አንዱ ሲያዜም ጣልቃ አትግባ፤ ተገቢ ባልሆነ ሰዓት ጥበብህን ለማሳየት አትሞክር። 5በወይን ጠጅ ግብዣ ላይ የሚታየ የሙዚቃ ትርኢት፥ በዕንቁ ላይ እንዳረፈ ወርቃማ ፈርጥ ነው። 6ከምርጥ የወይን ጠጅ ጋር የሚኮሞክሙት ሙዚቃ፥ ወርቃማ መደብ እንዳለው የከበረ ደንጊያ ነው። 7አንተ ወጣት! መናገር በሚገባህ ወቅት ተናገር፤ ቢበዛ ሁለት ጊዜ እርሱንም ከተጠየቅህ ብቻ አድርገው። 8ፍሬ-ሐሳቡን ብቻ ለመግለጽ ሞክር፥ በጥቂት ቃላት ብዙ መልእክት አስተላልፍ፤ ብዙ የምታውቅ፥ ንግግር ግን የማትወድ እንደሆንክ ሁነህ ቅረብ፤ 9ታላላቅ ሰዎን እንደ እኩዮችህ አትመልከት፤ ሌሎች ሲናገሩ የማይረባ አስተያየት አትስጥ። 10ከነጐድጓዱ በፊት ብልጭታው ቀድሞ እንደሚታይ፥ ከትሑት ሰው እንዲሁ ስጦታው ይቀድማል። 11ቀደም ብለህ ውጣ፤ የመጨረሻው ሰው አትሁን፥ ወዲያ ወዲህ ሳትል ወደ ቤትህም ሩጥ። 12ራስህን አዝናና፤ ያሻህንም አድርግ፤ ግትር በመሆን ግን በኃጢአት አትውደቅ። 13ስጦታዎች የለገሠህ፥ ይህን ሁሉ ያደረገልህን ፈጣሪ አመስግን።
እግዚአብሔርን መፍራት
14እግዚአብሔርን የሚፈራ ሁሉ እርምቱን ይቀበላል፤ እርሱን የሚሹ ሁሉ ጸጋውን ያገኛሉ። 15ሕጉን የሚከተል ሁሉ በእርሱ ይበለጽጋል፤ ለግብዞች ግን መሰናክል ነው። 16እግዚአብሔርን የሚፈሩ የእርሱን ቸርነት ያገኛሉ፤ መልካም ሥራቸውም እንደ ብርሃን ያበራል። 17ኃጢአተኛ ተግሣጽን አይቀበልም፤ ለፈጸመውም በደል ምክንያት አያጣም። 18አስተዋይ ሰው የሚነግሩትን ይሰማል፤ መጻተኞችና ትዕቢተኞች ፍርሃትን አያውቁም። 19ሳታስብ አታድርግ፤ በሠራኸውም አትጸጸትም። 20በመጥፎ መንገድ አትጓዝ፥ በድንጋይ ላይ ልትወድቅ ትችላለህና። 21በተስተካከለውም መንገድ አትተማመን፤ 22ከልጆችህም ተጠንቀቅ፤ 23በምታደርገው ነገር ሁሉ ራስህን ጠብቅ፤ ትእዛዛቱንም የምታከብርበት መንገድ ይኸው ነው። 24በሕጉ የሚያምን ደምቦቹን ያከብራል፤ እግዚአብሔርን የማያምን ሁሉ ከቶውንም ከጉዳት አይወድቅም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 32: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ