መጽሐፈ ሲራክ 31

31
ሀብት
1ሀብት የሚያመጣው የእንቅልፍ እጦት፤ ሰውነት ያከሳል፤ የሚያስከትለው ጭንቀትም እንቅልፍ ያባርራል። 2የቀኑ ጭንቀት አያስተኛም፤ እንደ ክፉ ደዌም እንቅልፍ ያሳጣል። 3ሀብትም ሁልጊዜ ይደክማል፤ ገንዘብ ያከማቻል፤ ሲያርፍም በምቾት ይንደላቀቃል። 4ድሀ ሁልጊዜ ይደክማል፤ ኑሮውም ከእጅ ወደ አፍ ነው፤ ሲያርፍም ይበልጥ ይደኸያል። 5ገንዘብ የሚወድ ከቶውንም ከኃጢአት አይነጻም፤ ትርፍ አሳዳጅም ከጥፋት ይወድቃል። 6ወርቅ ብዙዎችን አስቷል፤ ራሳቸውን ለጥፋት የዳረጉትም እነርሱ ናቸው። 7ለእርሱ መሥዋዕት የሚያቀርቡና አላዋቂዎች ሁሉ፥ በእርሱ ወጥመድ ይገባሉ። 8ወቀሳ የማይገኝበት፥ ለወርቅ ያላደረ ሀብታም የታደለ ነው። 9ከወገኖቹ መካከል እንዲህ የተደነቀው ማነው? እንኳን ደስ ያለህ ልንለው እንሻለን። 10ይህን ፈተና በአሸናፊነት የተወጣ ይኖራልን? ካለ ግን በእርግጥም ሊኮራ ይገባዋል! በኃጢአት መውደቅ ሲገባው ያልወደቀ፥ ማጥፋት ሲኖርበት ያላጠፋ ይገኛልን? 11ሀብቱ በጽኑ መሠረት ላይ ይገነባል፤ ጉባዔውም ደግነቱን ይመሰክርለታል።
የራት ግብዣዎች
12ከሚያስጐመዥ ማዕድ ፊት ስትቀርብ ስግብግብነትን አታሳይ፤ የሚበላው ተትረፍርፏልም አትበል። 13የዐይን ስስት የሚያስቀይም መሆኑን አትዘንጋ፤ በፍጥረት ውስጥ እንደ ዐይን የከፋ ነገር አለን? ሁሌም እንባ የሚያነባው ለዚህ ነው። 14የአስተናጋጅህ ዐይን ያረፈበትን ነገር አትንካ፤ ለማዕድ ስትቀርቡም አትጋፋው። 15የባልንጀራህን ፍላጐት እንደ ራስህ ፍረድ፤ በሁሉም መልክ አሳቢ ሁን። 16በሥርዓት እንዳደገ ሰው የቀረበልህን ተመገብ፤ ምግቡን አትጐስጐስ፤ መጠላት ታተርፋለህና። 17ትሕትህናን ቀድመህ መብላት በማቆም አስመስክር፤ ሰዎችን እንዳታስቀይም አጋቦስ አትሁን። 18ከብዙ ሰዎች ጋር ከተቀመጥህ ከሌሎቹ ቀድመህ እጅህን አትዘርጋ። 19መልካም አስተዳደግ ላለው የሚበቃው ትንሽ ነው፤ ሲተኛም በቀላሉ ይተነፍሳል። 20የተመጠነ ምግብ ጥሩ እንቅልፍ ይሰጣል፤ ንቁና ደስተኛም ያደርጋል፤ የአጋቦስ ትርፉ እንቅልፍ ማጣት፥ የሆድ ሕመምና የምግብ አለመፈጨት ነው። 21ብዙ ለመብላት ከተገደድህ ተነስ! ወጥተህም አስመልስ! ፈጥኖም ይሻልሃል። 22ልጄ ሆይ አትናቀኝ፥ እኔን አድምጠኝ፤ የቃሌንም ምንነት እያደር ትረዳለህ፤ በምታደርገው ሁሉ እርጋታ ይኑርህ፤ ሕመምም ጨርሶ አይነካህም። 23የተዋጣለት ግብዣ የሚያደርገውን ሰው፥ ሰዎች ያመሰግኑታል፤ ቸርነቱንም ያደንቃሉ። 24ንፉግ አስተናጋጅ ቅሬታን ያተርፋል፤ ሕዝቡም ክፋቱን ያወሩበታል።
ወይን ጠጅ
25ብዙ ሰዎችን ስላጠፋ ወይን ጠጅን አትድፈር። 26እሳት የብረት ጥንካሬ መፈተኛ እንደ ሆነው ሁሉ፥ የጉረኞችም ልበ-ደንዳናት መለኪያው የወይን ጠጅ ነው። 27በመጠኑ ከተጠጣ የወይን ጠጅ ሕይወት ነው። ሕይወት ያለ ወይን ጠጅ ትርጉሙ ምንድነው? የተፈጠረውም ሰዎችን ለማስደሰት ነው። 28በተገቢው ወቅትና በአስፈላጊው መጠን ከተጠጣ፥ የወይን ጠጅ የልብ ተድላና የነፍስ ደስታ ነው። 29የወይን ጠጅን በአጉል ድፍረት ከመጠን በላይ መጠጣት የነፍስ ምሬትን ያስከትላል። 30ስካር አላዋቂውን ያስቆጣል፤ ኃይሉን ይቀንስዋል፤ አምባጓሮም ውስጥ ይጨምረዋል። 31በወይን ጠጅ ግብዣ ላይ ጓደኛህን አትተንኩሰው፤ ደስ ባለው ሰዓት አትሳቅበት፤ በዚያን ሰዓት አትገሥጸው፤ ዕዳውንም ክፈል ብለህ አታበሳጨው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ