መጽሐፈ ሲራክ 30

30
የልጆች አስተዳደግ
1ልጁን የሚወድ ሁሉ አዘውትሮ ይቀጣዋል፤ ለወደፊትም በልጁ ይደሰታል። 2ልጁን የሚቆጣጠር የድካሙን ፍሬ ይሰበስባል፤ በሚያውቁት ሰዎችም ፊት በልጁ ይኮራል። 3ልጁን የሚያስተምር ጠላቱ ይቀናበታል፤ በወዳጆቹም መካከል በልጁ ይኮራል። 4አባቱ ቢሞት ሕያው ነው፤ መሳዩን ትቶ አልፏልና። 5በሕይወቱ ከልጁ ጋር ደስታን ተቋድሷል። ሞት በመጣ ጊዜም ስጋት የለበትም። 6ጠላቶቹን የሚበቀልበት፤ ወሮታውን የሚከፍልለት ልጅ ተክቷል። 7ልጅን የሚያንቀባርር ቁስሉን ይሸፈናል፤ ባለቀሰም ቍጥር አንጀቱ ይላወሳል። 8በደንብ ያልተገራ ፈረስ ያገረግራል፤ አግድም አደግ ልጅም አይታዘዝም። 9ልጅህን አሞላቅ፥ ያስደነግጥሃል። ከእርሱ ጋር ተጫወት፥ ያሳዝንሃል። 10አትሳቅበት፥ ያስለቅስሃል፥ ጥርስህንም ያስነክስሃል። 11በወጣትነቱ ነጻነት አትስጠው፤ ሲያጠፋም አትለፈው። 12በወጣትነቱ እንዲታዘዝህ ቅጣው፤ በልጅነቱ ጐን ጐኑን ሸንቁጠው። ካልተቀጣ ግን ግትርና ስድ ሆኖ ያድጋል፤ በጣምም ያሳዝንሃል። 13ልጅህን ተከታተል፥ ለአፍታም ቸል አትበለው፤ ካልሆነ ግን በአጥፊነቱ ትጸጸታለህ።
ጤና
14ጤነኛና ብርቱ ሆኖ መደኸየት፥ ሃብታም ሆኖ ከመሰቃየት ይሻላል። 15ከወርቅ ይልቅ ጤናና ብርታት፥ ከብዙ ሃብታም ጠንካራ አካል ይመረጣል። 16ከጤና የሚበልጥ ሃብት፥ ከመንፈስ ደስታም የሚበልጥ እርካታ የለም። 17ከመከራ ሕይወት ሞት፥ ከማይለቅ ደዌም ዘለለማዊ ዕረፍት ይሻላል። 18ለተዘጋ አፍ የሚቀርብ ጣፋጭ ምግብ፥ በመቃብር ላይ እንደሚቀርብ የምግብ መባ ነው። 19መብላትም ሆነ መጠጣት ለማይችል ጣዖት መሥዋዕት ማቅረብ ከቶ ምን ይጠቅማል? እግዚአብሔርም በደዌ የቀሰፈው ሰው እንዲሁ ነው። 20ቆንጆ ጉብል አቅፎ እንደሚያቃስ ጃንደረባ፥ እርሱም ያያል፥ ሲቃም ይይዘዋል።
ደስታ
21 # መክ. 11፥9፤10። ራስህን አታሳዝን፤ በሐሳብም አትጨነቅ። 22የልብ ደስታ ሕይወት ነው፤ የዕድሜም ምንጩ እርሱ ነው። 23ነፍስህን አስደስት፥ ልብህን አጽናና፥ ኀዘንን ከፊትህ አባርር፥ በእርሱ ምክንያት የብዙዎች ሕይወት ተበላሽቷል፤ ማንንም አይጠቅምምና። 24ቅናትና ቁጣ ዕድሜን ያሳጥራል፤ ጭንቀትም ያለ ዕድሜ ያስረጃል። 25ደስተኛ ልብ የምግብ አምሮትን ያዳብራል፤ መልካም አመጋገብንም ያስለምዳል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ