መጽሐፈ ሲራክ 3

3
ልጆች በወላጆቻቸው ፊት ያለባቸው ግዴታ
1ልጆች ሆይ! የኔን የአባታችሁን ምክር ስሙ። ለመዳን የምነግራችሁን ፈጽሙ፤ በእርሱም ተጠበቁ። 2ጌታ አባትን ከልጆቹ በላይ ያከብራል፤ የእናትንም መብት ከልጆችዋ በላይ ይጠብቃል። 3አባቱን የሚያከብር ኃጢአቶቹን ያስተሰርያል፤ 4እናቱን የሚያከብር ሃብት እንደሚያሰባስብ ሰው ነው። 5አባቱን የማያከብር በልጆቹ ደስታን ያገኛል፤ እርዳታን በለመነ ዕለት ጸሎቱ ይሰማል። 6አባቱን የሚያከብር ረጅም ዕድሜ ይኖረዋል፤ ለጌታ የሚታዘዝ እናቱን ደስ ያሰኛል፤ 7ጌቶችን እንደሚያገለግል ወላጆቹን ያገለግላቸዋል፤ 8#ዘፀ. 20፥12።የአባትህን ምርቃት ታገኝ ዘንድ፤ በቃልህም፥ በምግባርህም አክብረው። 9የአባት ምረቃ የልጆቹን ቤት ያጸናል፤ የእናት እርግማን ግን ሥርን ይነቅላል። 10በአባትህ ውርደት አትኩራ፤ የአባትህ ውርደት ላንተ ክብር አይደለም። 11የሰው ክብሩ የሚመነጨው ለአባቱ ካለው አክብሮት ነው፤ ክብሯን የማትጠብቅ እናትም ለልጆችዋ እፍረት ነች። 12ልጄ ሆይ በሸምግልና ዘመኑ አባትህን ደግፈው፤ በሕይወቱም ሳለ አታሳዝነው። 13አእምሮውን ቢስትም ራራለት፤ ጤነኛና ጠንካራ በመሆንህ እርሱን አትናቀው። 14ለአባትህ የዋልከው ደግነት አይዘነጋም፤ ለኃጢአትህ ይቅርታን ያስገኝለሃል እንጂ፤ 15በመከራ ጊዜ እግዚአብሔር ያስታውስሃል፤ ፀሐይ እንደመታው ውርጭ ኃጢአቶችህ ይቀልጣሉ። 16አባቱን የሚክድ አምላክን እንዳዋረደ ይቆጠራል። እናቱን የሚያሳዝን በጌታ የተረገመ ነው። 17ልጄ ሆይ የምትሠራውን ሁሉ፥ በደግነት አድርገው፤ ከፍተኛ ስጦታዎችን ከሚያበረክት ሰው አብልጦ ትወደዳለህ። 18#ፊልጵ. 2፥3።ታላቅነትህ ባደገ መጠን ትሕትናህም ይጨምር፤ ያንጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ታገኛለህ። 19#3፥19 አንዳንድ ጽሑፎች ቍጥር ዐሥራ ስምንትን እንደ ቍጥር ዐሥራ ዘጠኝ ያነቡታል። 20የእግዚአብሔር ሥልጣን ከፍ ያለ ቢሆንም፤ የትሑታኑን አክብሮት ይቀበላል። 21እጅግ የሚከብዱህ ነገሮችን ለማወቅ አትሞክር፤ ከአቅምህ በላይ ስለሆነ ነገር አትመራመር። 22#ዘዳ. 29፥29።በተሰጡህ ነገሮች ላይ አተኩር፤ ስለ ምሥጢራት አትጨነቅ፤ 23ከአቅምህ በላይ የሆኑት ጉዳዮች ውስጥ እጅህን አታስገባ። እስካሁን የተማርኸው ከሰው ልጅ አእምሮ አድማስ ይሰፋል። 24ብዙዎች በራሳቸው የተሳሳተ አመለካከት ተሰናክለዋል፤ መጥፎ አስተሳሰባቸው የኀሊና ፍርዳቸውን አዛብቶባቸዋል።
ትጋት
25ያለ ዐይን ብሌን ብርሃን አይኖርም፤ ያለ እውቀትም ጥበብ የለም። 26ሐሳበ ግትር አወዳዳቁ መጥፎ ነው፤ በአደጋ የሚጫወት ራሱን ያጣል። 27ሐሳበ ግትር መከራ ይበዛበታል፤ ኃጢአተኛ በኃጢአት ላይ ኃጢአት ይከምራል። 28የትዕቢተኛው ሕመም ፈውስ አይገኝለትም፤ ምክንያቱም የክፋት ተክል በሱ ውስጥ ሥር ሰዷል። 29አስተዋይ ልቦና ምሳሌዎችን ያሰላስላል፤ ንቁ ጆሮ የጥበበኛ ምኞት ነው።
ምጽዋት
30ውሃ የሚንበለበለውን እሳት እንደሚያጠፋ፥ እንዲሁም ምጽዋት ኃጢአትን ያነጻል። 31ለሰዎች የሚለግስ ሁሉ በምትኩ መጪውን ያስባል፤ ለመውደቅ ሲንገዳገድ ደጋፊ ያገኛል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ