መጽሐፈ ሲራክ 27

27
1ለትርፍ ሲሉ ብዙዎች በኃጢአት ወድቀዋል፥ ሃብታም ለመሆን የሚሻ እያየ እንዳላየ ይሆናል። 2ችካል በሁለት ድንጋዮች መካከል ሳይዛነፍ እንደሚቆም ሁሉ፥ በመሸጥና በመግዛትም መሀል እንዲሁ ኃጢአት ይገባል። 3እግዚአብሔርን በመፍራት ጸንቶ የሚይኖር ሁሉ፥ ሳይዘገይ ቤቱ ይፈርሳል።
ንግግር
4አሠር በወንፊት ላይ እንደሚቀር፥ የሰው ጉድለቱም እንዲሁ በንግግሩ ይንገዋለላል። 5የሸክላ ሠሪው ሥራ በእሳት፥ ሰውም በአነጋገሩ ይፈተናል። 6#ማቴ. 7፥17፤ 12፥33፤ ሉቃ. 6፥44።ዛፉ የሚበቅልበት የአትክልት ሥፍራ፥ በሚያፈራው ፍሬ ይመዘናል፤ የሰዎችንም ስሜት ቃላቸው ያጋልጣል። 7ቃሉን ሳትሰማ ሰውን አታሞግስ፤ ሰው የሚፈተነው በአነጋገሩ ነውና።
ጽድቅ
8ጽድቅን ብትከተል ታገኛታለህ፤ እንደ ክቡር ካባም ትጐናጸፋታለህ። 9ወፎች ከመሰሎቻቸው ጋር ይኖራሉ፤ እውነት ወደሚሿት ሰዎች ትመጣለች። 10አንበሳ ግዳይ ለመጣል ያደፍጣል፤ ኃጢአትም እንዲሁ በደለኞችን ያጠምዳል። 11የጻድቅ ሰው ንግግር ምንም ጊዜ ጥበብ ነው፤ ሞኝ ሰው ግን እንደ ጨረቃ ተለዋዋጭ ነው። 12ጅሎችን ስትጐበኝ ተገቢውን ሰዓት ምረጥ፤ ከአስተዋዮች ዘንድ ግን ስለ ጊዜ አታስብ። 13የሞኞችን ንግግር ያስቀይማል፤ በፈጸሙትም ኃጢአት እያጓሩ ይስቃሉ፤ 14መሐላ የሚያበዙ ሰዎች ንግግር ፀጉር ያቆማል፤ ጩኸታቸውም ጆሮ ያስይዛል፤ ስድባቸውም ለሰማ አስደንጋጭ ነው። 15የኩራተኞቹ ፍልሚያ በደም መፋሰስ ይደመደማል፤ እርግማናቸውም ለመስማት በጣም ያሳፍራል።
ምሥጢሮች
16 # ምሳ. 11፥13፤ 20፥19። ምሥጢሮችን የማይጠብቅ መታመንን ያጣል፤ የሚሻውንም ወዳጅ አያገኝም። 17ወዳጅህን ውደደው፥ እመነውም፤ ምሥጢሮቹን ካወጣህ ግን ዳግም አትቅረበው፤ 18ሰውን ገድሎ ማጥፋት እንደሚቻል ሁሉ፥ የጐረቤትህንም ወዳጅነት አንተ ገድለኸዋልና። 19ከእጅህ እንዳመለጠች ወፍ፥ እንዲሁ ባልንጀራህ አምልጦኃል፤ ዳግመኛም ልትይዘው አትችልም። 20አትከተለው፤ ከወጥመድ እንደምታመልጥ ሚዳቋም ሸሽቷል። 21ቁስል ይሸፍናል፤ ለስድብም ይቅርታ ይደረጋል፤ ምሥጢር ለሚያወጣ ግን አንዳች ተስፋ የለም።
ግብዝነት
22ዓይኑን የሚጨነቁር ተንኮል ያጠነናል፤ ይህን ከማድረግ የሚያግደው የለም። 23በፊትህ ንግግሩ አንደ ማር ይጣፋጣል፤ ያንተንም በአድናቆት ያዳምጣል። ከኋላህ የሚያወራው ግን ፈጽሞ ሌላ ነው፤ ቃልህንም መሰናክል ያደርገዋል። 24በርካታ ነገሮችን እጠላለሁ፤ እንደ እርሱ የሚሆን ግን ከቶ የለም፤ እግዚአብሔርም እርሱን ይጠላዋል። 25ድንጋይ የሚወረውር በራሱ ላይ ይጥለዋል፤ የክሕደት ቡጢ በሁለት አቅጣጫ ይቆርጣል። 26ጉድጓድ የሚቆፍር በውስጡ ይገባል፤ ወጥመድ ያጠመደም ራሱ ይጠመዳል። 27ክፉ በሚሠራ ክፉ ይወርድበታል፤ አመጣጡንም አያውቀውም። 28አሽሙርና ስድብ የግትር ሰው ምልክቶች ናቸው፤ በቀል ግን እንደ አንበሳ አድፍጦ ይጠብቀዋል። 29በጻድቅ ሰው ውድቀት በማደሰቱት ላይ ወጥመድ ይወድቅባቸዋል፥ ከሞታቸውም በፊት ሥቃይ ይጨርሳቸዋል።
ምሬት
30ምሬትና ቁጣ ከንቱ ነገሮች ናቸው፤ ኃጢአተኛውም ሰው በእነርሱ ሠልጥኗል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ