መጽሐፈ ሲራክ 22

22
ሀኬተኛ ሰው
1ሀኬተኛ ሰው በቁሻሻ እንደተሸፈነ ድንጋይ ነው፤ ሁሉም በቆሻሻነቱ ይንቀዋል፤ 2ሀኬተኛ ሰው እንደ ግፍ ነው፤ የሚነካው ሁሉ እጁን ያፈናጥቃል። መጥፎ ልጆች 3በጐ አስተዳደግ የጐደለው ልጅ አባት መሆን አሳፋሪ ነው፤ ሴት ልጅ መውለድ ግን ታላቅ ኪሣራ ነው። 4አስተዋይ ልጅ ባል ታገኛለች፤ እፍረተ ቢሷ ልጅ ግን የወላጅዋ ኀዘን ናት። 5ደፋር ሴት ልጅ እናትና አባቷን ታሳፍራለች፤ በሁለቱም ዘንድ ትተዋለች። 6ያለ ጊዜው የሚከሰት እምቢተኛነት በቀብር ላይ እንደሚሰማ ሙዚቃ ነው፤ ሁልጊዜ መቅጣትና ማረም ግን ጥበብ ነው።#22፥6 7-8. ያለ ችግር በመልካም አስተዳደግ የሚኖሩ ልጆች ወላጆቻቸው ከዝቅተኛ ቤተሰብ መምጣታቸውን ይረሳሉ። ግድየለሾች፥ አግድም አደጎችና ትዕቢተኛ ልጆች በወላጆቻቸው ጨዋነት ላይ ጥቁር ነጥብ ይጥላሉ።
ጥበብና ሞኝነት
9ሞኝን ማስተማር የተሰባበሩ ገሎችን እንደ መጠገን ነው፤ ጽኑ እንቅልፍ የያዘውንም ሰው እንደ መቀስቀስ ነው። 10ሞኝን ማስተማር ለተኛ ሰው እንደ ማውራት ነው፤ በጨረስህም ጊዜ ነገሩ ምንድነው? ይልሃል። 11ብርሃኑን ላጣው ለዚያ ለሞተ ሰው አልቅስ፤ አእምሮው ላጣው ለዚያ ለሞኝ ሰው አልቅስ። ለሞተውና ላረፈው ብዙ እንባ አታፍስ፤ የሞኝ ሕይወት ከሞት የከፋ ነውና። 12#ዘፍ. 50፥10፤ ዮዲ. 16፥24።ለሙታን የሚታዘነው ለሰባት ቀናት ነው፤ ለሞኞችና ለክፉዎች ግን ዕድሜ ልካቸውን ይታዘንላቸዋል። 13ከአላዋቂ ሰው ጋር ንግግር አታብዛ፤ ከጅልም አትጠጋ። እርሱን ተጠንቀቀው፥ አልያ ግን ችግር ላይ ትወድቃለህ። ከእርሱም ጋር በመነካካትህ ታድፋለህ። ከእርሱ ራቅ፥ የአእምሮ ሰላምም ታገኛለህ፤ በጅል ተግባሩም አትሸማቀቅም። 14ከእርሳስ የሚከብድ ምን አለ? ከሞኝ በቀር ሌላስ ስም አለውን? 15አሸዋ፥ ጨውና የብረት ቁራጭ ከጅል ሰው የቀለሉ ሸክሞች ናቸው። 16ከሕንጻው ጋር የተያየዘ ማገር መሬት ብትንቀጠቀጥም ቦታውን አይለቅም። አስቦበት የቆረጠ ልብም እንደዚሁ በቀውጢ ሰዓት አይብረከረክም። 17በበቃ ማስተዋል ላይ የተገነባ ልብ፥ በተስተካከለ ግድግዳ ላይ እንደሚደረግ ጌጥ ነው። 18በግምብ ላይ የተቀመጡ ጠጠሮች ንፋሱን መቋቋም አይችሉም፤ በገዛ ሐሳቡ ፍርሃት ያደረበት የሞኝ ልብም እንዲሁ ፍርሃትን አይቋቋምም።
ወዳጅነት
19ዐይን ብትጠነቁል እምባ ይፈሰዋል፥ ልብን ብተነካካው ደግሞ ስሜቶቹን ትገልጣለህ። 20በወፎች ላይ ድንጋይ ብትወረውር ታባርራቸዋልህ፤ ወዳጅህን ብትገሥጽ ደግሞ ወዳጅነትን ታጠፋለህ። 21በባልንጀራህ ላይ ሠይፍህን ብትመዝ፥ መመለሻ መንገድ ስላለው ተስፋን አትቁረጥ፤ 22ባልንጀራህ ላይ ክፉ ብትናገር እርቅ ይወርደ ዘንድ ተስፋ ስላለ አትጨነቅ፤ ብትሰድበው፥ ሐሳበ-ግትር ብትሆንበት፥ ምሥጢሩን ብትገልጽበትና ከጀርባው ብትወጋው ግን ባልንጀራህን እንደምታጣ እወቅ። 23ጐረቤትህ በደኸየ ጊዜ ታማኝነትህን አሳየው፥ ባገኘ ጊዜም አብረኸው መደሰት ትችላለህና። ከውርሱም ድርሻውን ታገኝ ዘንድ፤ በችግሩ ጊዜ ከጐኑ አትለይ። 24የእሳት መኖር በምድጃውና በጭሱ ጠረን እንደሚታወቀው፥ ደም መፍሰስም እንዲሁ በፀያፍ ቃል ይታወቃል። 25ባልንጀሪዬን ለማስጠጋት አላፍርም፤ ከእርሱም ፊት አልደበቅም። 26በእርሱም አማካኝነት ክፉ ቢደርስብኝ፤ ይህን የሰማ ሁሉ ከእርሱ ይጠነቀቃል።
ጸሎት
27በአፌ ላይ ዘብ የሚያቆም፤ በከንፈሮቼ ላይ የሚያትም፥ እንዳልወድቅና በምሳሌም ሰበብ እንዳልጠፋ የሚጠብቀኝ ከቶ ማን ይሆን?

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ