መጽሐፈ ሲራክ 21

21
ልዩ ልዩ ኃጢአቶች
1ልጄ ሆይ ኃጢአት አድርገሃልን? ዳግመኛ አታድርግ፥ ስላለፈውም ስሕተትህ ይቅርታ ጠይቅ። 2ከእባብ እንደምትሸሽ እንዲሁ ከኃጢአት ሽሽ፤ ከተጠጋህ ይነድፍሃል፤ ንጉሦቹ እንደ አንበሳ ጥርሶች ናቸው። የሰውንም ሕይወት ያጠፋሉ። 3ሕግን ማፍረስ በሁለት በኩል ስለት እንዳለው ሰይፍ ነው፤ በሰይፉ የተመታ ቁስሎቹ አይሽሩም። 4ሽብርና ዓመጽ ሃብትን ያምሳሉ፥ እንዲሁ የትዕቢተኛ ቤትም ይጠፋል። 5#ሲራ. 35፥17-19።የደኃን ልመና እግዚአብሔር ፈጥኖ ይሰማል፤ የእርሱም ፍርድ ሳይዘገይ ይደርሳል። 6ተግሣጽን የሚጠላ የኃጢአተኛን ፈለግ ይከተላል፤ ጌታን የሚፈራ ግን በልቡ ይጸጸታል። 7አፈ ጮሌው በሁሉም ዘንድ ይታወቃል፤ ጥንቁቅ ግን ምንም አያመልጠውም። 8በሌላ ሰው ገንዘብ ቤቱን የሚሠራ ለመቃብሩ ድንጋይ እንደሚሰበስብ ሰው ነው። 9የኃጢአተኞች ጉባኤ እንደ ገለባ ክምር ነው፤ ፍጻሜአቸው በሚንቦገቦግ እሳት ውስጥ ይሆናል። 10የኃጢአተኞች መንገድ ለስልሶ የተነጠፈ ነው፤ መጨረሻው ግን የሲኦል ጉድጓድ ነው።
ጥበበኛና ሞኝ ሰው
11ሕግን የማያከብር ሰው ሐሳቡን መቆጣጠር ይችላል፤ እግዚአብሔር መፍራት መጨረሻው ጥበበን ማግኘት ነው። 12ተፈጥሮአዊ ችሎታ የሚጐድለው ሰው ለመማር አይበቃም፤ አንዳንድ ክህሎቶች ግን ምሬትን ያመጣሉ። 13የጠቢቡ ዕውቀት እጅግ ጥልቅ፥ ምክሩም እንደማይደርቅ ምንጭ ነው። 14የሞኝ ልብ እንደ ሽንቁር ማሰሮ ነው። ምንም ዓይነት ትምህርት አይዝም። 15የተማረ ሰው የጥበብ ምሳሌ ሲሰማ ያደንቃል፤ የራሴንም ያክልበታል። ባካኝ ሰው ቢሰማው ግን አይወደውም፤ ሊያስታውሰውም አይሻም። 16የሞኝ ንግግር እንደ የመንገድ ላይ ሸክም ነው፤ አዋቂን ማድመጥ ግን ደስታ ነው። 17በጉባኤ ውስጥ የብልጡ ሰው ንግግር በጉጉት ይጠበቃል፤ ለንግግሩም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። 18የሞኝ ጥበብ እንደ ቤት ፍርስራሽ ያለ ነው፤ የማይረባ ሰው ዕውቀት ውል የሌለው ንግግር ነው። 19ለማያመዛዝን ሰው ትምህርት ሰው ትምርት በእግር ላይ እንደሚገባ እግረ-ሙቅ፥ በቀኝ እጅም ላይ እንደሚታሰር ሰንሰለት ነው። 20ሞኝ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጐ ይስቃል፤ አዋቂ ሰው ግን ያለ ድምፅ ፈገግ ይላል። 21ለአዋቂ ሰው ትምህርት እንደ ወርቅ ጌጥ፥ እንደ እጅ አምባርም ነው። 22ሞኝ ሰው እግሮቹን ወደ ቤት ለማስገባት ይጣደፋል፤ አዋቂ ሰው ግን በትሕትና ቀስ ብሎ ይገባል። 23ጋጠ-ወጡ በበር ቀዳዳ ያሾልቃል፥ ጨዋ ሰው ግን ከበር ይጠብቃል። 24በበር አጠገብ ቆሞ ማዳመጥ የመጥፎ አስተዳደግ ምልክት ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከቶውንም ይህን አያደርግም። 25የአሉባልተኞች ከንፈር ሌሎች የተናገሩትን ይደግፋል፤ የአዋቂ ሰው ንግግር የተመዘነ ነው። 26የሞኞች ልብ በአፋቸው፥ የአዋቂዎች አፍ ግን በልባቸው ውስጥ ነው። 27ክፉ ሰው ሰይጣንን ሲረግም ራሱን መርገሙ ነው። 28ሐሜተኛ ሰው ራሱን ያዋርዳል፤ የጐረቤቱቹንም ጥላቻ ያተርፋል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ