መጽሐፈ ሲራክ 1
1
የምሳሌዎች መድብል
የጥበብ ምንጭ
1 #
ምሳ. 2፥6። የጥበብ ሁሉ መገኛዋ ከጌታ ዘንድ ነው፥ ለዘለዓለምም ከእርሱ ጋር ናት። 2የባሕርን አሸዋ፥ የዝናምን ጠብታዎች፥ የዘለዓለምን ቀኖች፥ ማን ቆጥሮ ይዘልቃቸዋል? 3የሰማይን ምጥቀት፥ የምድርን ስፋት፥ የውቅያኖስን ጥልቀት፥ ማን መርምሮ አወቃቸው? 4ከፍጡሮች ሁሉ በፊት ጥበብ ተፈጠረች፤ 5ብሩህ ማስተዋል ከጥንት አንሥቶ ነበረች። 6የጥበብ ሥርዋ ለማን ተገለጠ? 7የጥበብንስ ዘዴና መንገድ ማን አወቃቸው? 8ጥበበኛ አንድ ብቻ ነው፥ እርሱም እጅግ ያስፈራል፤ በዙፋኑም ላይ ጸንቶ ይኖራል። 9#ምሳ. 8፥22-31፤ ሲራ. 24፥9።ጥበብን የፈጠራት ጌታ ራሱ ነው፤ ያያትና የመዘናትም እርሱ ነው፤ በሁሉም ሥራዎቹም ላይ አፈሰሳት። 10ለሁሉም ሕያው ፍጡር እርሱ እንደወደደው እሱን ለሚወድት ሰዎች ደግሞ እሷን አብዝቶ ሰጣቸው።
እግዚአብሔርን መፍራት
11ጌታን መፍራት ክብርና ኩራት ነው፤ ደስታና የሐሴት አክሊል ነው፤ 12ጌታን መፍራት ልብን ደስ ያሰኛል፤ ሐሴትንም ይሰጣል። ደስታንና ረጅም ሕይወትንም ይሰጣል። 13ጌታን የሚፈራ ሰው መጨረሻው ያምራል፤ በዕለተ ሞቱም ይባረካል። 14የጥበብ መጀመሪያዋ ጌታን መፍራት ነው፤ ለታማኞች በእናታቸው ማሕፀን ከነሱ ጋር ተፈጥራለች። 15በሰው ዘር ውስጥ ቤቷን መሥርታለች፤ የዘለዓለም መሠረትም ጥላለች፤ ከልጆቻቸው ጋር ታማኝ ሆና ትኖራለች፤ 16የጥበብ ምልአት ጌታን መፍራት ነው፤ በፍሬዎችዋ ሰዎችን ታረካቸዋለች፤ 17#ጥበ. 7፥11።ቤቶቻቸውንም በሀብት ትሞላለች፤ ጐተራዎቻቸውንም በምርቶችዋ ትሞላላቸዋለች፤ 18የጥበብ አክሊልዋ ጌታን መፍራት ነው፤ እርሷም ሰላምና ጤና እንዲያብቡ ታደርጋለች። 19እግዚአብሔር አይቷታል፥ መዝኗታል፤ እውቀትንና ማስተዋልን አዝንሟል፤ የሚያጸኗትንም ሰዎች ክብር ከፍ አደረገው። 20#ምሳ. 3፥16፤ 4፥10።የጥበብ ሥሩ ጌታን መፍራት ነው፤ ቅርንጫፎችዋም ረጅም ሕይወት ናቸው። 21እግዚአብሔርን መፍራት ኃጢአትን ያስወግዳል፤ በውስጡ ያደረበትም ቁጣን ሁሉ ያጠፋል።
ትዕግሥትና ራስን መግዛት
22የኃጢአተኛው ቁጣ ሊያጸድቀው አይችልም፤ የቁጣውም ክብደት ውደቀቱ ነውና። 23ትዕግሥተኛ ሰው ትክክለኛው ጊዜ እስኪደርስ ሁሉንም ይችላል፤ በስተመጨረሻ ግን ደስታን ያገኛል። 24እስከ ጊዜው ሐሳቦቹን ይዞ ይቆያል። ሕዝቡም ዓዋቂነቱን ይናገርለታል።
ጥበብና ትክክለኛነት
25በጥበብ መዝገቦች መካከል የዕውቀት ምሳሌዎች አሉ፤ ነገር ግን መንፈሳዊነት ለኃጢአተኛ የተናቀና የተጠላ ነው። 26ጥበብን ከፈለግህ ትእዛዛትን ጠብቅ፤ ጌታም የፈለግኸውን ይሰጥሃል። 27ጌታን መፍራት ጥበብና ትምህርት ነው፤ ታማኝነትና ደግነት እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነው። 28ጌታን ከመፍራት ውጭ አትሁን፤ ሁለትም ልብ ይዘህ ወደ እርሱ አትቅረብ፤ 29በሰዎች ፊት ጋባዥ አትሁን፤ ከንፈሮችህን ጠብቅ። 30እንዳትወድቅና በራስህ ላይ ውርደትን እንዳታመጣ ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ። ልብህ በተንኮል በመሞላቱና ጌታን ባለመፍራትህ እርሱ ምሥጢርህን ይገልጥብሃል፤ በሕዝቡም መሀል ያዋርድሀል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 1: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ