አማቷም ናዖሚ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። አሁንም ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። እንግዲህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፥ የክት ልብስሽንም ልበሺ፥ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። በሚተኛም ጊዜ፥ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም፦ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ወደ አውድማው ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፥ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፥ እነሆም፥ አንዲት ሴት በግርጌው ተኝታ ነበር። እርሱም፦ “ማን ነሽ?” አለ። እርሷም፦ “እኔ ባርያህ ሩት ነኝ፥ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባርያህ ላይ ጣል አለችው።” ቦዔዝም አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በጌታ የተባረክሽ ሁኚ፥ ባለ ጠጋ ይሁን ወይም ድሀ፥ ወጣቶችን መርጠሽ መሄድ አልፈለግሽምና ከፊተኛው ይልቅ አሁን ባደረግሽው ታማኝነትን አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።
መጽሐፈ ሩት 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሩት 3:1-11
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች