ወደ ሮሜ ሰዎች 16:17-27

ወደ ሮሜ ሰዎች 16:17-27 መቅካእኤ

ወንድሞች ሆይ! ከሚለያዩትና እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም መሰናክል ከሚያደርጉ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ፤ እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የገዛ ሆዳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉምና፤ በሚያሳምን ንግግርና በሽንገላ የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። መታዘዛችሁ በሁሉም ሰው ዘንድ ደርሶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። የሰላም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ ሥር ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉኪዮስ፥ ኢያሶንና ሶሲፓትሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ቴርትዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። እኔንና መላዋ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋዩስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው ገንዘብ ያዥ ኤራስቶስ፥ ወንድማችንም ኳርቶስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ በወንጌሌ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስብከት፥ ለዘመናት ተሰውሮ በነበረው የምሥጢር ግልፀት ሊያጸናችሁ ለሚችለው ለእርሱ፥ አሁን ግን ተገለጠ፤ በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ፥ አሕዛብ ሁሉ ለእምነት እንዲታዘዙ፥ በነቢያት መጻሕፍት እንዲያውቁት ተደርጓል፤ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።