የዮሐንስ ራእይ 3:3-16

የዮሐንስ ራእይ 3:3-16 መቅካእኤ

እንግዲህ ቃሉን እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስታውስ፤ ጠብቀውም፤ ንስሓም ግባ። ባትነቃ ግን እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ፤ በማናቸውም ሰዓት እንደምመጣብህ ከቶ አታውቅም። ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ። ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፤ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፤ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።” “በፊላደልፊያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ ‘ቅዱስና እውነተኛ የሆነው፥ የዳዊትም መክፈቻ ያለው፥ ሲከፍትም፥ ማንም የማይዘጋው፤ ሲዘጋም ማንም የማይከፍተው፤ እርሱ እንዲህ ይላል’፦ “ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ፤ ማንም ሊዘጋውም አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፤ ስሜንም አልካድህምና። እነሆ አይሁድ ሳይሆኑ ‘አይሁድ ነን’ ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ። የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ለመፈተን በዓለም ሁሉ ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ። እነሆ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ። ድል የሚነሣውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ወደፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለትም ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአዲሲቱን ኢየሩሳሌምን ስም፥ እንዲሁም አዲሱን ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ። መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ። “በሎዲቅያም ወዳለው ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፥ አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ የእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል፦ “ሥራህን አውቃለሁ፥ በራድ ወይም ትኩስ አለመሆንህን። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆን ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።