መዝሙረ ዳዊት 35:1-28

መዝሙረ ዳዊት 35:1-28 መቅካእኤ

አቤቱ፥ የሚከሱኝን ክሰሳቸው፥ የሚዋጉኝንም ተዋጋቸው። ጥሩርና ጋሻ ያዝ፥ እኔንም ለመርዳት ተነሥ። ሰይፍንና ጦርን ምዘዝ፥ የሚያሳድዱኝን ለመቃወም፥ ነፍሴን፦ መድኃኒትሽ እኔ ነኝ በላት። ነፍሴን ሊያጠፉ የሚሹ ሁሉ ይፈሩ ይጐስቁሉም፥ ክፉትን በእኔ ላይ የሚያስቡ ይዋረዱ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። በነፋስ ፊት እንዳለ ትቢያ ይሁኑ፥ የጌታም መልአክ ያስጨንቃቸው። መንገዳቸው ዳጥና ጨለማ ይሁን፥ የጌታም መልአክ ያሳድዳቸው። በከንቱ ያጠፉኝ ዘንድ ወጥመዳቸውን ሸሽገውብኛልና፥ ነፍሴን በከንቱ አበሳጭተዋልና። ያላወቁት ወጥመድ ይምጣባቸው፥ የሸሸጉትም ወጥመድ ይያዛቸው፥ በዚህ ወጥመድ ውስጥ ይውደቁ። ነፍሴ ግን በጌታ ደስ ይላታል፥ በማዳኑም ሐሴት ታደርጋለች። አጥንቶቼ ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ አቤቱ፥ እንደ አንተ ማን ነው? ችግረኛን ከሚቀማው እጅ፥ ችግረኛንና ድሀውንም ከሚነጥቀው እጅ ታድነዋለህ። የሐሰት ምስክሮች ተነሡብኝ፥ የማላውቀውንም በእኔ ላይ ተናገሩ። በበጎ ፈንታ ክፋትን መለሱልኝ፥ ለብቻዬም ቀረሁ። እኔስ እነርሱ በታመሙ ጊዜ ማቅ ለበስሁ፥ ነፍሴንም በጾም አደከምኋት፥ ጸሎቴም ወደ ብብቴ ተመለሰ። ለወዳጄና ለወንድሜ እንደማደርግ አደረግሁ፥ ለእናቱም እንደሚያለቅስ ራሴን ዝቅ ዝቅ አደረግሁ። በእኔ ላይ ተሰበሰቡ ደስም አላቸው፥ ግፈኞች በእኔ ላይ ተሰበሰቡ እኔም አላወቅሁም፥ መቦጫጨቃቸውን አላቆሙም። ፈተኑኝ በሣቅም ዘበቱብኝ፥ ጥርሳቸውንም በእኔ ላይ አንቀጫቀጩ። አቤቱ፥ እስከ መቼ ድረስ ዝም ብለህ ታየኛለህ? ነፍሴን ከክፉ ሥራቸው ብቸኛዪቱንም ከአንበሶች አድናት። አቤቱ፥ በታላቁ ጉባኤ ውስጥ እገዛልሃለሁ፥ በብዙ ሕዝብ መካከልም አመሰግንሃለሁ። ከሐዲ ጠላቶቼ በእኔ ደስ አይበላቸው፥ በከንቱ የሚጣሉኝም በዓይናቸው አይጠቃቀሱብኝ። በእርጋታ በምድሪቱ ለተቀመጡት ሰላምን አይናገሩምና፥ በቁጣም ሽንገላን ይመክራሉ። አፋቸውንም በእኔ ላይ አላቀቁ፥ እሰይ እሰይ፥ ዓይናችን አየው ይላሉ። አቤቱ፥ አንተ አየኸው፥ ዝም አትበል፥ አቤቱ፥ ከእኔ አትራቅ። አምላኬ ጌታዬም፥ ትፈርድልኝ ዘንድ ተነሥ፥ አቤቱ፥ ፍርዴን አድምጥ። አቤቱ አምላኬ፥ እንደ ጽድቅህ ፍረድልኝ፥ በእኔም ምክንያት ደስ አይበላቸው። በልባቸው፦ እሰይ እሰይ፥ ነፍሳችንን ደስ አላት አይበሉ፥ ደግሞም፦ ዋጥነው አይበሉ። በመከራዬ ደስ የሚላቸው ይፈሩ፥ በአንድነትም ይጐስቁሉ፥ በእኔ ላይ የሚታበዩ እፍረትንና ጉስቁልናን ይልበሱ። ጽድቄን የሚወድዱአት ደስ ይበላቸው ሐሴትንም ያድርጉ፥ የባርያውን ሰላም የሚወድድ ጌታ ታላቅ ይሁን ዘወትር ይበሉ። ምላሴ ጽድቅህን ሁልጊዜም ምስጋናህን ይናገራል።