ጥበብ ቤትዋን ሠራች፥ ሰባቱንም ምሰሶችዋን አቆመች። ፍሪዳዋን አረደች፥ የወይን ጠጅዋን አዘጋጀች፥ ማዕድዋን አሰናዳች። ሴቶች አገልጋዮችዋን ልካ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ ላይ ጠራች፦ “አላዋቂ የሆነ በዚህ በኩል ይለፍ፥” አእምሮ የጐደላቸውንም እንዲህ አለች፦ “ኑ፥ እንጀራዬን ብሉ፥ ያጣፈጥኩትንም የወይን ጠጅ ጠጡ። አላዋቂነትን ትታችሁ በሕይወት ኑሩ፥ በማስተዋልም መንገድ ሂዱ።” ፌዘኛን የሚገሥጽ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፥ ክፉንም የሚዘልፍ ኃፍረት ይገጥመዋል። ፌዘኛን አትገሥጽ እንዳይጠላህ፥ ጠቢብን ገሥጽ ይወድድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፥ ይበልጡን ጠቢብ ይሆናል፥ ጻድቅንም አስተምረው፥ ይበልጡን አዋቂ ይሆናል። የጥበብ መጀመሪያ ጌታን መፍራት ነው፥ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው። ዘመንህ በእኔ ይበዛልና፥ የሕይወትህም ዕድሜ ይጨመርልሃልና። ጠቢብ ብትሆን ለራስህ ጠቢብ ትሆናለህ፥ ፌዘኛም ብትሆን ፌዘኛነትህን ለብቻህ ትሸከማለህ። (የሚቀጥለው ከግሪክ የተጨመረ ነው።) ልጄ ለራስህ አዋቂ ብትሆን ለባልንጀራህም አዋቂ ትሆናለህ፥ ለራስህ ክፉ ብትሆን ግን ክፋትን ለብቻህ ትሸከማለህ። ሐሰትን የሚያዘጋጅ ሰው ነፋሳትን እንደሚገዛ ነው፥ የሚበርር ወፍንም እንደሚከተል ይመስላል። የወይኑ ቦታ መንገዱን ረስቷልና፥ የሚሠማራባትን መንገድ እንዲስት አድርጓልና፥ ወደ ምድረ በዳ ይሄዳል፥ ለጥም ወደ ተሠራች አገር ይሄዳል፥ የማያፈራ የማይጠቅም ገንዘብንም በእጁ ይሰበስባል። አላዋቂ ሴት ሁከተኛ ናት፥ አሳብ የላትም፥ አንዳችም አታውቅም። በቤትዋ ደጅ በከተማይቱ ከፍተኛ ስፍራ በወንበር ላይ ትቀመጣለች፥ በመንገድ የሚያልፉትን አካሄዳቸውንም ያቀኑትን ለመጥራት፦ “አላዋቂ የሆነ በዚያ ይለፍ፥” አእምሮ የጐደለውንም እንዲህ አለች፦ “የስርቆት ውኃ ይጣፍጣል፥ የተሸሸገም እንጀራ ደስ ያሰኛል።” ነገር ግን እርሱ ሙታን ከዚያ እንዳሉ፥ ተጋብዦችዋም በሲኦል ጥልቀት ውስጥ እንዳሉ አያውቅም።
መጽሐፈ ምሳሌ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ምሳሌ 9:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች