መጽሐፈ ምሳሌ 11:1-16

መጽሐፈ ምሳሌ 11:1-16 መቅካእኤ

የሐሰት ሚዛን በጌታ ፊት አስጸያፊ ነው፥ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል። ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፥ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች። ቅኖች ቅንነታቸው ትመራቸዋለች፥ ወስላቶችን ግን ጠማማነታቸው ታጠፋቸዋለች። በቁጣ ቀን ሀብት አትረባም፥ ጽድቅ ግን ከሞት ታድናለች። የፍጹም ሰው ጽድቁ መንገዱን ያቀናለታል፥ ክፉ ግን በክፋቱ ይወድቃል። ቅኖችን ጽድቃቸው ይታደጋቸዋል፥ ወስላቶች ግን በምኞታቸው ይጠመዳሉ። ክፉ ሰው በሞተ ጊዜ ተስፋው ይቈረጣል፥ የኃያል አለኝታም ይጠፋል። ጻድቅ ከጭንቀት ይድናል፥ ክፉ ግን የእርሱን ቦታ ይወስዳል። እኩይ ሰው በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፥ ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ። በጻድቃን ልማት ከተማ ደስ ይላታል፥ በክፉዎችም ጥፋት እልል ትላለች። በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፥ በክፉዎች አፍ ግን ትገለበጣለች። ወዳጁን የሚንቅ ልበ ጐደሎ ነው፥ አስተዋይ ሰው ግን ዝም ይላል። ለሐሜት የሚሄድ ምሥጢሩን ይገልጣል፥ በመንፈስ የታመነ ግን ነገሩን ይሰውራል። መልካም ምክር በሌለበት ሕዝብ ይወድቃል፥ በአማካሪዎች ብዛት ግን ዋስትና ይገኛል። ለእንግዳ ሰው የሚዋስ ክፉ መከራን ይቀበላል፥ ዋስ መሆንን የሚጠላ ግን ይድናል። ሞገስ ያላት ሴት ክብርን ታገኛለች፥ ኃያላንም ሀብትን ያገኛሉ።።