ወደ ፊልሞና 1:4-18

ወደ ፊልሞና 1:4-18 መቅካእኤ

በጸሎቴ እያሰብኩህ ሁልጊዜ አምላኬን አመሰግናለሁ። በጌታ በኢየሱስ ዘንድ፤ በቅዱሳንም ሁሉ ዘንድ ስላለው ፍቅርህና እምነትህ እሰማለሁና። የእምነትህም ኅብረት፥ በእኛ ዘንድ ያለውን በጎ ነገር ሁሉ በማወቅ፥ ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍሬ እንዲያፈራ እለምናለሁ፤ የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ ወንድሜ ሆይ! በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። ስለዚህ የሚገባውን አዝህ ዘንድ በክርስቶስ ምንም እንኳ ብዙ ድፍረት ቢኖረኝ፥ ይልቁንም እንደዚህ የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ሽማግሌው፥ አሁንም ደግሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እስረኛ የሆንሁ፥ ስለ ፍቅር እለምናለሁ። በእስራቴ ስለ ወለድሁት ስለ ልጄ ስለ ኦኔሲሞስ እለምንሃለሁ፤ በፊት አልጠቀመህም ነበር፤ አሁን ግን ለእኔም ለአንተም በጣም እየጠቀመን ነው። እርሱን እልከዋለሁ፤ አንተም ልቤ እንደምትቀበል አድርገህ ተቀበለው። እኔስ ስለ ወንጌል በገጠመኝ እስራት አንተን ወክሎ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው በፈቅድኩ ነበር፤ ነገር ግን በጎነትህ በፈቃድህ እንጂ በግድ እንዳይሆን፥ ሳልማከርህ ምንም ነገር ላደርግ አልፈልግሁም። ዳግመኛ ተቀብለህ ለዘለዓለም እንድትይዘው ይሆናል ምናልባት ለጊዜው የተለየህ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እንደ ባርያ አይሆንም፤ ነገር ግን ለእኔ በተለየ የተወደደ ወንድም ከሆነ፥ ለአንተማ ይልቅ በሥጋውም ሆነ በጌታ ዘንድ ከባርያ የሚሻል የተወደደ ወንድም እንዴት አይሆንም? እንግዲህ እንደ ወንድምህ እስከ ቆጠርከኝ ድረስ፥ እንደ እኔ አድርገህ ተቀበለው። በአንዳች ነገር በድሎህ እንደሆነ ግን ወይም ብድር ያለበት እንደሆነ፥ ይህን በእኔ ላይ ቁጠር፤