ኦሪት ዘኍልቊ 24

24
የበለዓም ሦስተኛው ትንቢት
1በለዓምም ጌታ እስራኤልን መባረክ ደስ እንደሚያሰኘው ባየ ጊዜ፥ አስቀድሞ ያደርግ የነበረውን አስማት ለመሻት አልሄደም፤ ነገር ግን ወደ ምድረ በዳ ፊቱን አቀና። 2በለዓምም ዓይኑን አንሥቶ እስራኤል በየነገዱ ተቀምጦ አየ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ። 3እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥
ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
4የእግዚአብሔርን ቃላት የሚሰማ፥
ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥
ወድቆም ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦
5ያዕቆብ ሆይ! ድንኳኖችህ፥
እስራኤል ሆይ! ማደሪያዎችህ ምንኛ ያምራሉ!
6ወደፊትም ተዘርግቶ እንዳለው ሸለቆች፥
በወንዝ ዳር እንዳሉ አትክልቶች፥
ጌታ እንደ ተከለው ዓልሙን
በውኃም ዳር እንዳሉ ዝግባዎች ተዘርግተዋል።
7ከማድጋዎቹ ውኃ ይፈስሳል፥
ዘሩም በብዙ ውኆች ይሆናል፥
ንጉሡም ከአጋግ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፥ መንግሥቱም ይከበራል።
8እግዚአብሔርም ከግብጽ አውጥቶታል፤
ጉልበቱ አንደ ጎሽ ቀንድ ያለ ነው፤
ጠላቶቹን አሕዛብን ይበላል፥
አጥንቶቻቸውንም ይሰባብራል፥
በፍላጾቹም ይወጋቸዋል።
9 # ዘፍ. 49፥9፤ ዘፍ. 12፥3። እንደ አንበሳ ዐርፎ ተኝቶአል፥
እንደ እንስቲቱም አንበሳ ተጋድሞአል፤
ማን ያስነሣዋል?
የሚባርክህ ሁሉ የተባረከ ይሁን፥
የሚረግምህም ሁሉ የተረገመ ይሁን።”
10የባላቅም ቁጣ በበለዓም ላይ ነደደ፤ እጆቹንም አጨበጨበ፤ ባላቅም በለዓምን እንዲህ አለው፦ “ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ ጠራሁህ፥ እነሆም፥ ሦስት ጊዜ ፈጽመህ ይኸው ባረክሃቸው፤ 11እንግዲህ አሁን ወደ ስፍራህ ሽሽ፤ እኔም እንዲህ አልሁ፦ ‘በእውነት አከብርህ ዘንድ ወድጄ ነበር፤’ ጌታ ግን፥ እነሆ፥ ክብርህን ከለከለህ።” 12በለዓምም ባላቅን እንዲህ አለው፦ “አንተ ወደ እኔ ለላክሃቸው መልእክተኞችህ እንዲህ ብዬ ነግሬአቸው አልነበረምን? 13‘ባላቅ በቤቱ የሞላውን ብርና ወርቅ ቢሰጠኝ፥ በራሴ ፈቃድ መልካምን ወይም ክፉን ነገር ለማድረግ የጌታን ቃል መተላለፍ አልችልም፤ ጌታ የተናገረውን እርሱን እናገራለሁ።’ 14እነሆ፥ አሁን፥ ወደ ሕዝቤ እሄዳለሁ፤ ና፥ ይህ ሕዝብ በሚመጣው ዘመን በሕዝብህ ላይ የሚያደርገውን እነግርሃለሁ።”
የበለዓም አራተኛው ትንቢት
15እርሱም ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“የቢዖር ልጅ በለዓም እንዲህ ይላል፥
ዐይኖቹ የተከፈቱለት ሰው እንዲህ ይላል፤
16የጌታን ቃላት የሚሰማ፥
የልዑልንም እውቀት የሚያውቅ፥
ሁሉን የሚችል የአምላክን ራእይ የሚያይ፥
ወድቆ ሳለ ዐይኖቹ ግን የተከፈቱለት እንዲህ ይላል፦
17አየዋለሁ፥ አሁን ግን አይደለም፤
እመለከተዋለሁ፥ በቅርብ ግን አይደለም፤
ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፥
ከእስራኤልም በትረ መንግሥት ይነሣል፥
የሞዓብንም ግንባር ይመታል፥
የሤትንም ልጆች ያጠፋል።
18ኤዶምያስም ርስቱ ይሆናል፥
ጠላቱ ሴይር ደግሞ ርስቱ ይሆናል፤
እስራኤልም በኃይል ያደርጋል።
19ከያዕቆብም የሚወጣ ገዥ ይሆናል፥
ከከተማውም በሕይወት የተረፉትን ያጠፋል።”
20በለዓምም አማሌቅን አይቶ ምሳሌውን ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“የአሕዛብ መጀመሪያ የሆነ አማሌቅ ነበረ፤
ፍጻሜው ግን ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።”
21ቄናውያንንም አይቶ ምሳሌውን ይምስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“ማደሪያህ የጸና ነው፥
ጎጆህም በዐለት ላይ ተሠርቶአል፤
22ቄናዊው ግን ለጥፋት የተዘጋጀ ይሆናል። አሦር የሚማርክህ እስከ መቼ ድረስ ይሆን?”
23ምሳሌውንም ይመስል ጀመር፥ እንዲህም አለ፦
“እግዚአብሔር ይህን ባደረገ ጊዜ
ወዮ! ማን በሕይወት ይኖራል?
24ከኪቲም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፥
አሦርንም ያሠቃያሉ፥
ዔቦርንም ያስጨንቃሉ፤
እርሱም ደግሞ ወደ ጥፋት የሚያመራ ይሆናል።” 25በለዓምም ተነሣ፥ ተመልሶም ወደ ስፍራው ሄደ፤ ባላቅም መንገዱን ተከትሎ ወደ ቤቱ ሄደ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ