ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያንና ከኢየሩሳሌም የመጡ አንዳንድ ጸሐፍት በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ ባልነጻ ማለትም ባልታጠበ እጅ እንጀራ ሲበሉ አዩ፤ ፈሪሳውያንና አይሁድ ሁሉ የአባቶችን ወግ ለመጠበቅ ሲሉ፥ በሥርዓቱ መሠረት እጃቸውን በጥንቃቄ ሳይታጠቡ አይበሉም ነበርና። ከገበያ ሲመለሱም ታጥበው ራሳቸውን ካላነጹ በስተቀር አይበሉም ነበር። እንዲሁም ዋንጫን፥ ማሰሮን፥ ሳሕንና ዐልጋን እንደማጠብ ያሉትን ሌሎችን ወጎች ይጠብቁ ነበር። ፈሪሳውያንና ጸሐፍትም፥ “ደቀ መዛሙርትህ እንደ አባቶች ወግ በመኖር ፈንታ ባልታጠበ እጃቸው ለምን እንጀራ ይበላሉ?” ብለው ጠየቁት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ኢሳይያስ ስለ እናንተ፥ ስለ ግብዞች ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነው፤ በከንቱ ያመልከኛል፤ ትምህርታቸውም ሰው ሠራሽ ሥርዓት ብቻ ነው። ተብሎ እንደ ተጻፈ በእውነት ትንቢት ተናገረ። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ የሰዎችን ወግና ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። ደግሞም፥ እንዲህ አላቸው፤ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ፥ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የምትተውበት ዘዴ። ሙሴ፥ አባትህንና እናትህን አክብር፤ አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ ፈጽሞ ይሙት ብሎ ነበርና፤ እናንተ ግን አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን፥ ከእኔ ማግኘት የሚገባችሁን ርዳታ ሁሉ ቁርባን ይኸውም መባ አድርጌለሁ ቢላቸው፥ እናንተም ይህ ሰው ለአባቱም ሆነ ለእናቱ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም። ስለዚህ ለትውልድ በምታስተላልፉት ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ፤ ይህን የመሰለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።” ደግሞም ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ስሙኝ፤ ሁላችሁም አስተውሉ፤ ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን የሚያረክሰው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁን ሰውን የሚያረክሰው ከራሱ ወደ ውጭ የሚወጣው ነገር ነው፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።” ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ከገባ በኋላ ደቀመዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ጠየቁት። እርሱም፥ “እናንተም ነገሩ አይገባችሁምን? ከውጭ ወደ ሰው ገብቶ ሊያረክሰው የሚችል አንዳች ነገር የለም፤ ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ይገባል፤ ከዚያም ከሰውነቱ ይወጣልና። ኢየሱስ ይህን በማለቱ ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን ገለጸ። ቀጥሎም፥ እንዲህ አለ፤ ከሰው የሚወጣ ያ ሰውን ያረክሰዋል፤ ከውስጥ፥ ከሰው ልብ የሚወጡት ክፉ ሐሳብ፥ ምንዝር፥ ስርቆት፤ ሰው መግደል፥ ዝሙት፥ መስገብገብ፥ ክፋት፥ ማታለል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስም ማጥፋት፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸው። እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ይወጣሉ ሰውንም ያረክሱታል።” ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጢሮስ አገር ሄደ፤ ወደ አንድ ቤት ገብቶ እዚያ መኖሩን ማንም እንዳያውቅበት ፈለገ፤ ሆኖም እዚያ መኖሩ ሊሸሸግ አልቻለም። ወዲያው ግን ትንሺቱ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እርሱ ሰምታ መጣችና በእግሩ ላይ ወደቀች። ሴትዮዋም ግሪካዊት፥ በትውልዷም ሲሮፊኒቃዊት ነበረች። እርሷም ኢየሱስ ርኩስ መንፈሱን ከልጇ እንዲያስወጣላት ለመነችው። እርሱ ግን፥ “የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መጣል ተገቢ ስላልሆነ፥ መጀመሪያ ልጆቹ ጠግበው ይብሉ” አላት። እርሷም መልሳ፥ “አዎን፥ ጌታ ሆይ፤ ውሾችም ከገበታ በታች ሆነው የልጆችን ትራፊ ይበላሉ” አለችው። እርሱም፥ “ስለዚህ ይህን ስላልሽ ሂጂ፤ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷአል” አላት። እርሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ ዐልጋ ላይ ተኝታ፥ ጋኔኑም ለቋት አገኘቻት።
የማርቆስ ወንጌል 7 ያንብቡ
ያዳምጡ የማርቆስ ወንጌል 7
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የማርቆስ ወንጌል 7:1-30
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች