የማርቆስ ወንጌል 2:3-12

የማርቆስ ወንጌል 2:3-12 መቅካእኤ

አራት ሰዎችም አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው አመጡለት። ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ወደ እርሱ ማቅረብ ስላልቻሉ፥ እርሱ ያለበትን የቤቱን ጣራ አነሡ፤ ነድለውም ሽባው የተኛበትን አልጋ አወረዱ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “አንተ ልጅ! ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤” አለው። በዚያም ተቀምጠው ከነበሩ አንዳንድ ጻሐፍት በልባቸውም “ይህ ሰው ስለምን እንደዚህ ያለ ስድብ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአት ሊያስተሰርይ ማን ይችላል፤” ብለው አሰቡ። ኢየሱስም በልባቸው እንዲህ እንዳሰቡ በመንፈስ ወዲያው አውቆ እንዲህ አላቸው “በልባችሁ ይህን ስለምን ታስባላችሁ? ሽባውን ‘ኃጢአትህ ተሰርዮልሃል፤’ ከማለትና ‘ተነሣ አልጋህንም ተሸከምና ሂድ፤’ ከማለት የቱ ይቀላል? ነገር ግን ለሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ሊያስተሰርይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፤” ብሎ ሽባውን፦ “አንተን እልሃለሁ፥ ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ፤” አለው። እርሱም ተነሥቶ ሁሉም እያዩት ወዲያው አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች