የማቴዎስ ወንጌል 5:27-48

የማቴዎስ ወንጌል 5:27-48 መቅካእኤ

“‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ወደ ሴት አይቶ የተመኛት ሁሉ ከወዲሁ በልቡ ከእርሷ ጋር አመንዝሮአል። ቀኝ ዐይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ከአንተ ቆርጠህ ጣላት፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከሰውነትህ አንዱ ክፍል ቢጠፋ ይሻልሃልና። “‘ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ የፍቺ ወረቀት ጽሕፈት ይስጣት’ ተብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በዝሙት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፤ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል። “ደግሞም ለቀደሙት ‘በውሸት አትማል ነገር ግን የማልኸውንም ለጌታ ስጥ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በፍጹም አትማሉ፤ በሰማይ አትማሉ የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤ በምድርም አትማሉ የእግሩ ማረፊያ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አትማሉ የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤ በራስህም አትማል፤ አንዲቱን ጠጉር እንኳ ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና። ስለዚህ ንግግራችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከእነዚህ የተረፈ ግን ከክፉው ነው። “‘ዐይን ስለ ዐይን፥ ጥርስ ስለ ጥርስ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ክፉውን አትቃወሙት፤ ነገር ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ ሊከስህ ፈልጎ እጀ ጠባብህን ሊወስድ የፈለገ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤ ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ እንድትሄድ ቢያስገድድህ፥ ሁለት ምዕራፍ ከእርሱ ጋር ሂድ። ለሚጠይቅህ ስጥ፤ ከአንተ ሊበደር ከሚፈልገው ፊትህን አታዙር። “‘ባልንጀራህን ውደድ፥ ጠላትህን ጥላ’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ ይህን በማድረግ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች እንድትሆኑ ነው፤ እርሱ ለክፉዎችና ለደጎች ፀሐዩን ያወጣልና፥ ለጻድቃንና ለኃጥኣንም ዝናቡን ያዘንባልና። የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ሽልማት ታገኛላችሁ? ቀራጮች እንኳ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁን ብቻ ሰላም የምትሉ ከሆነ ምን የበለጠ ነገር ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ይህንኑ ያደርጉ የለምን? ስለዚህ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ እናንተም ፍጹማን ሁኑ።

ተዛማጅ ቪዲዮዎች